መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 4
4
ኤልሳዕ ድሃዪቱን ሴት እንደ ረዳት
1ከነቢያትም ልጆች የአንዱ ሚስት የሆነች አንዲት ሴት፥ “ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳም ሁለቱ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል” ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች። 2ኤልሳዕም፥ “አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽም ያለውን ንገሪኝ” አላት። እርስዋም፥ “ለእኔ ለአገልጋይህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም” አለችው። 3እርሱም፥ “ሂጂና ከጎረቤቶችሽ ሁሉ ከውጭ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ፤ አታሳንሻቸውም። 4ወደ ቤትሽም ገብተሽ ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፤ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ” አላት። 5እንዲሁም ከእርሱ ሄዳ፥ በሩን ከእርስዋና ከልጆችዋ በኋላ ዘጋች፤ እነርሱም ማድጋዎቹን ወደ እርስዋ ያቀርቡላት ነበር፤ እርስዋም ትገለብጥ ነበር። 6ከዚህም በኋላ ልጆችዋን፥ “ደግሞ ማድጋ አምጡልኝ” አለቻቸው፤ እነርሱም፥ “ሌላ ማድጋ የለም” አሏት፤ ዘይቱም ቆመ። 7መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፤ እርሱም፥ “ሄደሽ ዘይቱን ሽጭ ዕዳሽንም ክፈዪ፤ በተረፈውም ዘይት የአንቺንና የልጆችሽን ሰውነት አድኚ” አላት።
ኤልሳዕና ሱማናዊት ሴት
8ከዚህም በኋላ አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱማን አለፈ፤ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራም ይበላ ዘንድ አቆመችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር። 9ሴትዮዋም ለባልዋ፥ “ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ። 10ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋና ጠረጴዛ፥ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይግባ” አለችው። 11አንድ ቀንም ወደዚያ በመጣ ጊዜ ወደ ቤቱ ገብቶ በዚያ ተኛ። 12ሎሌውንም ግያዝን፥ “ይህችን ሱማናዊት ጥራ” አለው። በጠራትም ጊዜ በፊቱ ቆመች። 13እርሱም፥ “እነሆ፥ ይህን ሁሉ ክብር አከበርሽኝ ምን ላድርግልሽ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ የምነግርልሽ ጉዳይ እንዳለሽ በላት” አለው፤ እርስዋም፥ “እኔ በወገኔ መካከል እኖራለሁ” ብላ መለሰች። 14እርሱም ግያዝን፥ “እንግዲህ ምን እናድርግላት?” አለው። ሎሌው ግያዝም፤ “ልጅ የላትም፥ ባልዋም ሸምግሎአል” ብሎ መለሰ። 15እርሱም፥ “ጥራት” አለው። ጠራትም በደጃፉም ቆመች። 16ኤልሳዕም፥ “በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት፤ እርስዋም፥ “አይደለም ጌታዬ ሆይ፥ አገልጋይህን አትዋሻት” አለችው። 17ከዚያም በኋላ ሴቲቱ ፀነሰች፥ በዓመቱም ኤልሳዕ በነገራት ወራት ወንድ ልጅ ወለደች።
18ሕፃኑም አደገ፤ እህል አጫጆችም ወዳሉበት ወደ አባቱ መጣ። አባቱንም፥ “ራሴን ራሴን” አለው፤ 19አባቱም ሎሌውን፥ “ተሸክመህ ወደ እናቱ ውስደው” አለው። 20አንሥቶም ወደ እናቱ ወሰደው፤ በጕልበቷም ላይ እስከ ቀትር ድረስ አስተኛችው፤ ሞተም። 21አውጥታም በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አጋደመችው፤ በሩንም ዘግታበት ወጣች። 22ባልዋንም ጠርታ፥ “ወደ እግዚአብሔር ሰው ዘንድ በፍጥነት እሄዳለሁና አንድ ሎሌና አንድ አህያ ላክልኝ” አለችው። 23እርሱም፥ “መባቻ ወይም ሰንበት ያይደለ ዛሬ ለምን ትሄጃለሽ?” አለ። እርስዋም፥ “ደኅና ነው” አለች። 24አህያውንም አስጭና ሎሌዋን፥ “ንዳ፥ ሂድ፤ እኔ ሳላዝዝህ አታዘግየኝ፤ ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ቄርሜሎስ ተራራ እንሂድ” አለችው።
25እንዲሁም ሄደች፤ ወደ እግዚአብሔርም ሰው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣች። ኤልሳዕም ያችን ሴት ወደ እርሱ ስትመጣ ባያት ጊዜ ሎሌውን ግያዝን፥ “እነኋት፥ ሱማናዊት መጣች፤ 26አሁንም ሩጥና ተቀበላት፤ በደኅናሽ ነውን? ባልሽ ደኅና ነውን? ልጅሽስ ደኅና ነውን? በላት” አለው። እርስዋም፥ “ደኅና ነው” አለች። 27ወደ ተራራውም ወደ ኤልሳዕ ደርሳ እግሮቹን ጨበጠች፤ ግያዝም ሊያርቃት መጣ፤ ኤልሳዕም፥ “ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያን ከእኔ ሰውሮታል፤ አልነገረኝምም” አለ። 28እርስዋም፥ “በውኑ ከጌታዬ ልጅን ለመንሁን? እኔም አታታልለኝ አላልሁህምን?” አለች። 29ኤልሳዕም ግያዝን፥ “ወገብህን ታጠቅ፤ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሂድ፤ ሰውም ብታገኝ ሰላም አትበል፤ እርሱም ሰላም ቢልህ አትመልስለት፤ በትሬንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኑር” አለው። 30የሕፃኑም እናት፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ሕያው ነፍስህንም! አልተውህም” አለች፤ ኤልሳዕም ተነሥቶ ተከተላት። 31ግያዝም በፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ግያዝም ቀድሞአቸው ደረሰ፤ በትሩንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኖረው፤ ነገር ግን ድምፅ ወይም መስማት አልነበረም፤ እርሱንም ሊገናኘው ተመልሶ፥ “ሕፃኑ አልተነሣም” ብሎ ነገረው።
32ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ ሕፃኑ ሞቶ በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር። 33ኤልሳዕም ወደ ቤት ገብቶ በሩን በሁለቱ ላይ ዘጋ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። 34መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ አፉንም በአፉ፥ ዐይኖቹንም በዐይኖቹ፥ እጆቹንም በእጆቹ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ሰውነት ሞቀ። 35ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ከዚያም በኋላ ሕፃኑ ዐይኖቹን ከፈተ። 36ግያዝንም ጠርቶ፥ “ይህችን ሱማናዊት ጥራ” አለው። ጠራትም፤ ወደ እርሱም በገባች ጊዜ፥ “ልጅሽን አንሥተሽ ውሰጂ” አላት። 37ሴትዮዋም ገብታ በእግሩ አጠገብ ወደቀች በምድርም ላይ ሰገደች፤ ልጅዋንም አንሥታ ወጣች።
ኤልሳዕ ሌሎች ሁለት ተአምራትን እንደ አደረገ
38ኤልሳዕም ዳግመኛ ወደ ጌልጌላ ተመለሰ፤ በምድርም ላይ ራብ ነበረ፤ የነቢያትም ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፤ ኤልሳዕም ሎሌውን፥ “ታላቁን ምንቸት ጣድ፤ ለነቢያትም ልጆች ቅጠላ ቅጠል አብስልላቸው” አለው። 39አንዱም ቅጠላ ቅጠል ያመጣ ዘንድ ወደ ሜዳ ወጣ፤ በምድረ በዳውም የወይን ቦታ አገኘ፤ ከዚያም የምድር ቅጠላ ቅጠል ሰብሰበ፤ ልብሱንም ሞላ፤ መትሮም በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ አበሰለውም፤ ምን እንደ ሆነ ግን አላወቁም። 40ከዚህም በኋላ ሰዎቹ ይበሉ ዘንድ አቀረበላቸው፤ የበሰለውንም ቅጠል በሚበሉበት ጊዜ፥ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ በምንቸቱ ውስጥ መርዝ አለ” ብለው ጮኹ፤ ይበሉም ዘንድ አልቻሉም። 41ኤልሳዕም፥ “ዶቄት አምጣና በምንቸቱ ውስጥ ጨምረው” አለው፥ ኤልሳዕም ግያዝን፥ “ለሕዝቡ መልስላቸው ይብሉ” አለው። ከዚህም በኋላ በምንቸቱ ውስጥ ክፉ ነገር አልተገኘም።
42አንድ ሰውም ከቤትሣሪሳ ከእህሉ ቀዳምያት፥ ሃያ የገብስ እንጀራ፥ የእህልም እሸት በአቁማዳ ይዞ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ፤ ኤልሳዕም አገልጋዩን፥ “ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው” አለ። 43ሎሌውም፥ “ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው አቀርባለሁ?” አለ። እርሱም፥ “ይበላሉ፥ ያተርፋሉም ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው” አለው። 44እርሱም አቀረበላቸው፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል በሉ፤ አተረፉም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ