በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስከ ሞት ድረስ ታመመ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም ሰማው፤ ምልክትም ሰጠው። ሕዝቅያስ ግን እግዚአብሔር እንደ ሰጠው ቸርነት መጠን አላደረገም፤ ልቡም ኮራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ ቍጣ ሆነ። ሕዝቅያስም በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኵራት ሰውነቱን አዋረደ፤ እግዚአብሔርም በሕዝቅያስ ዘመን ቍጣውን አላመጣባቸውም። ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቍና ለሽቱው፥ ለጋሻውና ውድ ለሆነው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶችን ሠራ። ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንስሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ። እግዚአብሔርም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ለራሱ ሠራ፤ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ። ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፤ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። ሕዝቅያስም በሥራው ሁሉ ተከናወነ። ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በሀገሩ ላይ ስለ ተደረገው ተአምራት ይጠይቁት ዘንድ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ እግዚአብሔር ይፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ያውቅ ዘንድ ተወው። የሕዝቅያስም የቀሩት ነገሮች፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትም ሁሉ በሞቱ አከበሩት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 32 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 32:24-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች