መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 2
2
ቤተ መቅደስን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት
(1ነገ. 5፥1-18)
1ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስም ቤት፥ ለራሱም ቤተ መንግሥት ልሥራ አለ። 2ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም ድንጋዮችን የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ሰበሰበ። 3ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ፥ “ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ይሠራ ዘንድ የዝግባ እንጨት እንደ ላክህለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ። 4እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘለዓለም እንደ ታዘዘው በእግዚአብሔር ፊት የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን ለማጠን፥ የገጹንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር በዓላት ለማቅረብ እኔ ልጁ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራለሁ፤ እርሱንም እቀድሳለሁ። 5አምላካችን እግዚአብሔርም ከአማልክት ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ ነው። 6ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ ክብሩን ይሸከም ዘንድ አይችልምና ለእርሱ ቤት ይሠራ ዘንድ ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 7አሁንም በወርቅና በብር፥ በናስና በብረት፥ በሐምራዊና በቀይ፥ በሰማያዊም ግምጃ መለበጥ የሚችልና፥ አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር ቅርጽ ማውጣት የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰውን ላክልኝ። 8ደግሞም አገልጋዮችህ ከሊባኖስ እንጨት መቍረጥ እንዲያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ፥ የሰንደልም እንጨት ላክልኝ። 9የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ክቡር ይሆናልና ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኝ ዘንድ፥ እነሆ፥ አገልጋዮች ከአገልጋዮችህ ጋር ይወጣሉ። 10እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለአገልጋዮችህ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሃያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሃያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሃያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት በነጻ እሰጣለሁ።”
11የጢሮስ ንጉሥ ኪራምም፥ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ወድዶአልና በላያቸው አነገሠህ” ሲል ለሰሎሞን ጻፈለት። 12የጢሮስ ንጉሥ ኪራምም ደግሞ አለ፥ “ለእግዚአብሔር ቤት ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ ጥበበኛና ብልሃተኛ፥ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ፥ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን። 13አሁንም ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው አቢኪራምን ልኬልሃለሁ። 14እናቱ ከዳን ልጆች ናት፤ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ በወርቅና በብር፥ በናስና በብረት፥ ድንጋዩንና እንጨቱን መለበጥ፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ መሥራት፥ ቅርጽም፥ ሌላም ነገር ሁሉ ማድረግ ያውቃል። ከብልሃተኞችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር ሥራ ብለህ የምትሰጠውን ሁሉ አስቦ መሥራት ይችላል። 15አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደ አገልጋዮቹ ይላክ፤ 16እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፤ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እንልካለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።”
17ሰሎሞንም አባቱ ዳዊት ከቈጠራቸው ጋር ያልተቈጠሩ በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ ሰበሰበ፤ ቍጠራቸውም መቶ ኀምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሆኖ ተገኘ። 18ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮቹም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ በሕዝቡም ሥራ ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ አደረገ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 2: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ