ኤልያስም የበዓልን ነቢያት፥ “እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፤ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፤ በበታቹም እሳት አትጨምሩ” አላቸው። የተሰጣቸውን ወይፈንም ወስደው አዘጋጁ፤ ከጥዋትም እስከ ቀትር ድረስ፥ “በዓል ሆይ፥ ስማን፥” እያሉ የበዓልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፤ የሚመልስም አልነበረም፤ የሠሩትንም መሠዊያ እያነከሱ ይዞሩ ነበር። በቀትርም ጊዜ ቴስብያዊው ኤልያስ፥ “አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት ይጫወት ይሆናል፥ ወይም አሳብ ይዞት ይሆናል፥ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል” እያለ ይዘባበትባቸው ጀመር። በታላቅም ቃል ይጮኹ ጀመር፤ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በጦርና በሰይፍ ይብዋጭሩ ነበር። እስከ ሠርክም ድረስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፤ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም። ከዚህም በኋላ መሥዋዕት በሚያርግበት ጊዜ ኤልያስ ነቢያተ ሐሰትን፥ “እንግዲህስ ወዲያ በቃችሁ፤ ወግዱ፤ ሂዱም፥ እኔም መሥዋዕቴን እሠዋለሁ” አላቸው። ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ፥ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ኤልያስም፦ ስምህ እስራኤል ይሆናል የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ እስራኤል ልጆች ነገድ ቍጥር ዐሥራ ሁለት ድንጋዮችን ወሰደ። ድንጋዮችንም በእግዚአብሔር ስም መሠዊያ አድርጎ ሠራቸው፤ የፈረሰውንም መሠዊያ አደሰ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚይዝ ጕድጓድ ቈፈረ። በሠራውም መሠዊያ ላይ እንጨቱን ደረደረ፤ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቈረጠ፤ በእንጨቱም ላይ አኖረ፤ “አራት ጋን ውኃ አምጡልኝ፤ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይም አፍስሱ” አለ፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ደግሞም፥ “ድገሙ” አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም፥ “ሦስተኛ አድርጉ” አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ። ውኃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ። ደግሞም ጕድጓዱን በውኃ ሞላው። ነቢዩ ኤልያስም ወደ ሰማይ አቅንቶ ጮኸ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ ስማኝ፤ ጌታዬ ሆይ፥ ዛሬ በእሳት ስማኝ፤ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፤ ይህንም ሥራ ስለ አንተ እንዳደረግሁ እነዚህ ሕዝቦች ይወቁ። አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ፤ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፤ አቤቱ፥ ስማኝ” አለ። እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወረደች፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ እንጨቱንም፥ ድንጋዮቹንም በላች፤ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ፥ አፈሩንም ላሰች።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 18 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 18:25-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos