ትንቢተ ሶፎንያስ 3

3
የእስራኤል ክፋት
1ለዓመፀኛዪቱና ለረከሰች፥ ለጨቋኞች ከተማ ወዮላት! 2ማንንም አታዳምጥም፥ እርምት አትቀበልም፥ በጌታ አልታመነችም፥ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም። 3በውስጧ የሚኖሩ ባለ ሥልጣኖቿ የሚያገሡ አንበሶች ናቸው፥ ፈራጆችዋም ለጠዋት ምንም የማያስቀሩ የማታ ተኩላዎች ናቸው። 4ነቢዮችዋ ስዶችና ከሐዲ ሰዎች ናቸው፥ ካህናቶቿ መቅደሱን አርክሰዋል፥ በሕግም ላይ አምፀዋል። 5በውስጧ ያለው ጌታ ጻድቅ ነው፥ ስሕተት አያደርግም፥ ማለዳ ማለዳ ፍርዱን ለብርሃን ይሰጣል፥ አያቋርጥምም፤ ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም። 6መንግሥታትን አጥፍቻለሁ፥ ግንቦቻቸው ሁሉ ፈርሰዋል፥ መንገዶቻቸውን ማንም የማይተላለፍባቸው ባዶ ሆነዋል፥ ከተሞቻቸውም አንድም ሰው እንዳይገኝባቸው፥ ማንም የማይኖርባቸው ሆነዋል። 7እኔም አልኩ “በእርግጥ ትፈሪኛለሽ፥ እርማትንም ትቀበያለሽ፤ መኖሪያዋ አይጠፋም፥ ያቀድኩትም አይደርስም።” እነርሱ ግን በማለዳ ተነሥተው ድርጊታቸውን ሁሉ አረከሱ።
የመንግሥታት መቀጣትና መመለስ
8ስለዚህ “ጠብቁኝ” ይላል ጌታ፤ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ፥ ፍርዴ ሕዝቦችን ለመሰብሰብ፥ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነው፥ ይህም መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ ለማፍሰስ ነው፤ በቅንዓቴ እሳት ምድርም ሁሉ ትበላለችና።
9በዚያን ጊዜም ሁሉም የጌታን ሥም እንዲጠሩና በአንድ ትከሻ እንዲያገለግሉት፥ ለሕዝቦች ንጹሕን አንደበት እመልስላቸዋለሁ። 10ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚያመልኩኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቁርባኔን ያመጡልኛል። 11በዚያ ቀን በእኔ ላይ አምፀሽ በሠራሽው ሥራ ሁሉ አታፍሪም፤ በኩራትሽ የተደሰቱትን ከመካከልሽ አወጣለሁና፥ አንቺም በቅዱስ ተራራዬ ላይ ዳግመኛ አትታበዪም። 12በመካከልሽ ትሑትና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በጌታም ስም ይታመናሉ። 13#ራእ. 14፥5።የእስራኤል ትሩፍ ኃጢአትን አይሠሩም፥ ሐሰትንም አይናገሩም፥ በአፋቸውም ውስጥ አታላይ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፥ ይተኛሉ፥ የሚያስፈራቸውም የለም።
የደስታ መዝሙር
14የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በሉ፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሴት አድርጊ ደስም ይበልሽ። 15ጌታ ቅጣትሽን አስወግዷል፥ ጠላትሽንም አጥፍቷል፤ የእስራኤል ንጉሥ ጌታ በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አትፈሪም። 16በዚያን ቀን ኢየሩሳሌም እንዲህ ይባልላታል፦ “ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ። 17ጌታ አምላክሽ በመካከልሽ ኃያል ታዳጊ ነው፤ በአንቺም በፍጹም በደስታ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል።” 18ከበዓሉ ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር። 19እነሆ በዚያ ዘመን፥ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ። 20በዚያ ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ በሰበሰብኳችሁም ጊዜ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ