የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 11

11
የዛፎች፥ የእረኞችና የአንበሶች ለቅሶ
1ሊባኖስ ሆይ፥ ደጆችህን ክፈት፥ እሳትም ዝግባዎችህን ትብላ! 2የጥድ ዛፍ ሆይ፥ ዝግባ ወድቆአልና፥ የከበሩትም ዛፎች ጠፍተዋልና አልቅሱ! እናንተም የባሳን ዛፎች ሆይ፥ ጽኑው ጫካ ተቈርጦአልና አልቅሱ! 3የእረኞች ክብር ተዋርዶአልና የዋይታቸውን ድምፅ ስሙ! የዮርዳኖስ ጥቅጥቅ ደን ወድሟልና የአንበሶች ግሣት ድምፅ ስሙ!
የእረኞች ትረካ
4 # ሕዝ. 34፥1፤ ኤር. 12፥3። አምላኬ ጌታ እንዲህ ብሏል፦ ለእርድ የሚሆኑትን በጎች ጠብቅ። 5የገዙአቸው ያርዱአቸዋል፥ እንደ በደለኞች አይቆጠሩም፥ የሸጧቸውም፦ “ባለ ጠጋ ሆኛለሁ፤ ጌታ ይመስገን!” ይላሉ። እረኞቻቸው እንኳን አይራሩላቸውም። 6ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖሩ አልራራም፥ ይላል ጌታ፤ እነሆም፥ ሰውን ሁሉ ለባልንጀራውና ለንጉሡ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱንም ይመታሉ፥ ከእጃቸውም አላስጥላቸውም።
7እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፤ የአንዲቱን ስም “ደስታ” የሁለተኛይቱንም ስም “አንድነት” ብዬ ጠራሁ፤ መንጋውንም አሰማራሁ። 8በአንድ ወር ጊዜም እኔንም ስለሰለቹኝ፥ እነርሱም ስለጠሉኝ፥ ሦስቱን እረኞች አስወገድኩ። 9እኔም፦ “እናንተን አልጠብቅም፤ የሚሞተው ይሙት፥ የሚጠፋውም ይጥፋ፤ የቀሩትም እርስ በእርሳቸው ተበላልተው ይጨራረሱ።” አልሁ።
10እኔም ከሕዝቦች ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን ለማፍረስ “ደስታ” የተባለችውን በትሬን ወስጄ ሰበርኳት። 11በዚያም ቀን ኪዳኑ ፈረሰ፤ እንዲሁም እኔን ሲመለከቱ የነበሩ የተጨነቁ መንጋዎች የጌታ ቃል እንደ ነበረ አወቁ። 12#ማቴ. 27፥3-10፤ 2ነገ. 12፥11፤ 22፥4።እኔም፦ “ደስ ብሎአችሁ እንደሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፥ ያለዚያ ግን ተውት” አልኩት። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ። 13ጌታም፦ ሊከፍሉኝ የተስማሙበት ጥሩ ዋጋ በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በጌታ ቤት ባለው ግምጃ ክፍል ውስጥ አኖርኩት። 14ከዚያም በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውንም ወንድማማችነት ለመለያየት “አንድነት” የተባለቸውን ሁለተኛይቱን በትሬን ሰበርኳት።
15 # ሕዝ. 34፥1-10። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ አሁን እንደገና የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ። 16#ኢሳ. 42፥3፤ ማቴ. 12፥20።እነሆ፥ በአገር ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስተውልም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፥ የዳነውንም አይቀልብም፤ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል።
ለማይረቡ እረኞች ትንቢት
17 # ኤር. 23፥1፤ ዮሐ. 10፥12-13። መንጋውን ለሚተው ለማይረባ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ ክንዱንና ቀኝ ዓይኑን ይውጋው፤ ክንዱም ፈጽማ ትሰልስል፤ ቀኝ ዓይኑም ፈጽማ ትታወር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ