የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 1

1
ለተአዝዞ የቀረበ ጥሪ
1ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ በስምንተኛው ወር፥ የጌታ ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2#ሚክ. 3፥7።ጌታ በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር። 3ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል ወደ እኔ ተመለሱ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።” 4#ኢሳ. 55፥7፤ ሉቃ. 20፥15።የቀደሙት ነቢያት ለአባቶቻችሁ እንዲህ ብለው ሰብከዋል፦ “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤’” እነርሱ ግን አልሰሙም፤ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፥ ይላል ጌታ። 5አባቶቻችሁ ወዴት ናቸው? ነቢያትስ ለዘለዓለም በሕይወት መኖር የሚችሉ ይመስላችኋልን? 6#ዘካ. 7፥7-14።ነገር ግን ለአገልጋዮቼ ለነቢያት ያዘዝኳቸው ቃሎቼና ሥርዓቴ በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሱምን? ከዚያ እነርሱም ተጸጽተው፦#1፥6 በዕብራይስጥ “ተመልሰው” ይላል። “የሠራዊት ጌታ በመንገዳችንና በሥራችን መጠን ሊያደርግብን ያሰበውን እንዲሁ አድርጎብናል” በማለት ተቀበሉ።
የመጀመሪያው ራእይ፦ ምድርን የሚዞሩ ፈረሶች
7 # ዘካ. 6፥1-7፤ ራእ. 5፥6፤ 6፥1-9። ዳርዮስ በነገሠ ሁለተኛው ዓመት፥ ሳባጥ በሚባል በዓሥራ አንደኛው ወር፥ በሀያ አራተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ በራክዩ ልጅ፥ ወደ አዶ ልጅ፥ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦
8እነሆ፥ አንድ ሰው በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጦ በሌሊት አየሁ፥ እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ነበር፤ በስተ ኋላውም ቀይና ነጭ አንባላይም ፈረሶች ነበሩ። 9እኔም፦ “ጌታዬ፥ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልኩት። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ፦ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ። 10#ዘካ. 7፥5፤ ኤር. 25፥11-12፤ 29፥10።በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረው ሰው፦ “እነዚህ ምድርን እንዲያስሱ ጌታ የላካቸው ናቸው” ብሎ መለሰ። 11እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ለነበረው ለጌታ መልአክ፥ “ምድርን አሰስናት፥ እነሆም፥ መላዋ ምድር በጸጥታ ዐርፋ ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት። 12#ራእ. 6፥10።የጌታም መልአክ መልሶ፦ “አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ፥ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ። 13ጌታም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው።
ንግራዊ ምላሽ
14 # ዘካ. 8፥2። ስለዚህም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፥ ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ በታላቅ ቅንዓት በኢየሩሳሌምና በጽዮን ቀንቻለሁ። 15#ኢሳ. 47፥6።እኔ ብዙም ሳልቆጣቸው እነርሱ ክፋትን ስላገዙት፥ በምቾት በሚኖሩት አሕዛብ ላይ እጅግ ተቈጥቻለሁ። 16#ኢሳ. 54፥6-10፤ ዘካ. 2፥5-9።ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ፤ ቤቴ መልሶ ይገነባባታል፤ በኢየሩሳሌምም ላይ መለኪያ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 17#ዘካ. 2፥15፤ 13፥9።ደግሞም እንዲህም ስትል ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ እንደገና በብልጽግና ይሞላሉ፤ ጌታም እንደገና ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ምርጫው ያደርጋታል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ