መጽሐፈ ጦቢት 2
2
2 የጦቢት መታወር
1 #
ዘፀ. 23፥16። በንጉሥ ኤሳራዶን ዘመን ወደ ቤቴ ተመለስሁ፥ ሚስቴን ሐናንና ልጄን ጦቢትንም መልሰው አመጡልኝ። የሳምንቶች በዓል በሆነው በጴንጤቆስጤ በዓላችን ቀን መልካም እራት ተዘጋጀልኝ፥ እኔም ለመብላት ተቀመጥሁ፤ 2ምግቡ ቀረበልኝ፥ የተትረፈረፈ ምግብ እንደቀረበልኝ ባየሁ ጊዜ ልጄን ጦብያን እንዲህ አልሁት፦ “ልጄ ሆይ ሂድና ወደ ነነዌ ተማርከው ከመጡት ወንደሞቻችን መካከል የሆኑትንና ታማኝ ልቦና ያላቸውን ድኻ የሆኑትን ሰዎች ፈልግና ከማዕዴ እንዲካፈሉ አምጣቸው፤ ልጄ ሆይ እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ።” 3ጦቢያ ከወንድሞቻችን መካከል ድኻ ለመፈለግ ሄደ፤ ግን ተመልሶ መጣና “አባቴ” አለኝ፤ እኔም “ምንድነው ልጄ?” አልሁት፤ እሱም “አባቴ ከወገኖቻችን አንዱ ተገድሎ በገበያ ተጥሎአል፤ በታነቀበት እዛው ወድቋል” አለኝ። 4ምንም ሳልቀምስ፥ እራቴን ትቼ ተነስቼ ሄድሁ ሰውዬውን ከአደባባይ አነሳሁት፥ ፀሐይ ስትጠልቅ ለመቅበር ሬሳውን ከክፍሎቼ በአንዱ አኖርሁት። 5#ዘኍ. 19፥11-13።ወደ ቤቴ ተመለስሁ፥ ታጠብሁና ምግቤን እያዘንሁ በላሁ። 6#አሞጽ 8፥10።ነቢዩ አሞፅ የቤተልን ሰዎች፦ “በዓላችሁ ወደ ኀዘን፥ መዝሙራችሁ ወደ ለቅሶ ይለወጣል” ያለውን አስታወስሁ። 7እኔም አለቀስሁ። ፀሐይ በጠለቀች ጊዜ ሄድሁና ጉድጓድ ቆፈርሁ ቀበርሁትም። 8ጐረቤቶቼ ሳቁብኝ እንዲህም አሉ፦ “ይህ ሰው ምንም አይፈራም፤ እንዲህ ያለ ሥራ በመስራቱ ሊገድሉት ፈልገው ሸሽቶ አምልጦ ነበር፤ አሁንም የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ይቀብራል።” 9በዚያች ሌሊት ታጠብሁና ከግቢው አጥር ስር ተኛሁ፤ ሙቀት ስለ ነበረ ፊቴን አልሸፈንሁትም። 10በግንቡ ላይ ድንቢጦች መኖራቸውን አላወቅሁም ነበር፤ ትኩስ ኩሳቸውም በዐይኖቼ ላይ ወደቀብኝና ነጭ ነጥብ ሆነ፤ ለመታከም ወደ ሐኪሞች ሄድሁ፥ ግን መድኃኒት ባደረጉልኝ ቍጥር ነጥቦቹ እየተጨመሩ ሄዱና ጭራሹን ታወርሁ። ለአራት ዓመታት ማየት አልቻልሁም፤ ዘመዶቼም በኔ ነገር በጣም ያዝኑ ነበር፤ አሂካር ወደ ኤሊማይስ እስከሄደበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመታት ተንከባከበኝ። 11በዚያን ጊዜ ሚስቴ ሐና በሴቶች ሥራ ሱፍ በመፍተልና ልብስ አድርጋ በመሥራት ገንዘብ አገኘች። 12የታዘዘችውን ሰርታ ታስረክባለች እነሱም ይከፍሏታል። በዲስትሮስ ሰባት አንድ ልብስ ሠርታ ጨረሰችና ለደንበኞቿ አስረከበች፤ እነሱም የሚገባትን ከከፈልዋት በኋላ በተጨማሪ ለእርድ አንድ የፍየል ጠቦት ሰጡዋት። 13ፍየልዋ ወደ ቤቴ በመጣች ጊዜ መጮህ ጀመረች፤ እኔም ሚስቴን ጠራሁና “ይህች ፍየል ከየት መጣች? ምናልባት በስርቆት መጥታ ይሆናል፥ ወደ ባለቤቶችዋ መልሰሽ ውሰጃት፤ በስርቆት የመጣ ነገር መብላት አንችልምና” አልኳት። 14እርሷም “ከደሞዜ በተጨማሪ የተሰጠችኝ ሥጦታ ናት” አለችኝ። እኔ ግን አላመንኳትም፥ ለባለቤቶችዋ እንድትመልስ ነገርኳት፥ በእስዋም በጣም አፈርሁ፤ እርሷም “አንተ ያደረግሃቸው ምጽዋቶች የት አሉ? መልካም ሥራዎችህስ ሁሉ የት አሉ? እነዚህን በጎ ተግባራት በመፈጸምህ ያገኘኸው ምን እንደሆነ ሁሉም ሰው ያውቃል።” ስትል መለሰች።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጦቢት 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ