የዮሐንስ ራእይ 7
7
በእግዚአብሔር ማኅተም ስለታተሙ መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች
1 #
ኤር. 49፥36፤ ዳን. 7፥2፤ ዘካ. 6፥5። ከዚህም በኋላ በአራቱ የምድር ማዕዘን የቆሙ አራት መላእክት አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ላይም ቢሆን ወይም በባሕር ላይ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ። 2የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፤ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ 3#ሕዝ. 9፥4፤6።“የአምላካችንን ባርያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርንም ሆነ ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ፤” አላቸው። 4የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። 5ከይሁዳ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፤ ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ 6ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ 7ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ 8ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።
ከየነገዱ የተሰበሰቡ ብዙ ሕዝቦች
9ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሰዎች ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ 10በታላቅም ድምፅ እየጮሁ
“ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!”
አሉ። 11መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ
12“አሜን ውዳሴ፥ ክብር፥ ጥበብ፥ ምስጋና ገናናነት፥ ክብር
ኃይልና ብርታት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ለአምላካችን
ይሁን! አሜን።”
አሉ።
13ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ “እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከየትስ መጡ?” አለኝ። 14#ዳን. 12፥1፤ ማቴ. 24፥21፤ ማር. 13፥19።እኔም “ጌታ ሆይ! አንተ ታውቃለህ፤” አልሁት። እንዲህም አለኝም፦ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሶቻቸውንም አጥበው በበጉ ደም አንጽተዋል። 15ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ይቆማሉ፤ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ውስጥ ያመልኩታል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በእነርሱ ላይ ይዘረጋል። 16#ኢሳ. 49፥10።ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፤ ፀሐይም ሆነ ትኩሳትም ሁሉ ከቶ አይመታቸውም፤ 17#መዝ. 22፥1፤ ሕዝ. 34፥23፤ መዝ. 22፥2፤ ኢሳ. 49፥10፤ ኢሳ. 25፥8።በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ