የዮሐንስ ራእይ 14:14-20

የዮሐንስ ራእይ 14:14-20 መቅካእኤ

ከዚያም አየሁ፤ እነሆም ነጭ ደመና በደመናውም ላይ የሰው ልጅን የሚመስል ተቀምጦአል፤ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው። ሌላም መልአክ ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው “የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፤ የምድሪቱ መከር ደርሶአልና፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፤ ምድርም ታጨደች። ሌላም መልአክ በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፤ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው። በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን “ዘለላዎቹ በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቁረጥ፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ተጣራ። መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፤ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር የቁጣ ወይን መጥመቂያ ጣለ። የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፤ እስከ ፈረሶች ልጓም የሚደርስና እስከ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ድረስ የሚርቅ ደም ከመጥመቂያው ወጣ።