አቤቱ፥ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ። በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቆሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ። በጩኸት ደከምሁ ጉሮሮዬም ሰለለ፥ አምላኬን ስጠብቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ። በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጉር በዙ፥ በዓመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፥ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ። አቤቱ፥ አንተ ቅብጠቴን ታውቃለህ፥ ጥፋቴም ከአንተ አልተሰወረም። አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ የሚሹህ በእኔ አይነወሩ። ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፥ እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና። ለወንድሞቼ እንደ ሌላ፥ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው። የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና። ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ። ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው። በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፥ ሰካራሞች በእኔ ላይ ይዘፍናሉ። አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፥ አቤቱ፥ በቸርነትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ። እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፥ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ። የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ፥ ጥልቁም አይዋጠኝ፥ ጉድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ። አቤቱ፥ ቸርነትህ መልካም ናትና ስማኝ። እንደ ርኅራኄህም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፥ ከባርያህም ፊትህን አትሰውር፥ ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ መልስልኝ። ወደ ነፍሴ ቀርበህ ተቤዣት፥ ስለ ጠላቶቼም አድነኝ። አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፥ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው። ስድብ እስክታመም ድረስ ልቤን ሰበረው፥ አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም፥ የሚያጽናናኝም አጣሁ።
መዝሙረ ዳዊት 69 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙረ ዳዊት 69:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች