መዝሙረ ዳዊት 37:12-30

መዝሙረ ዳዊት 37:12-30 መቅካእኤ

ክፉ በጻድቁ ላይ ያደባል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያንገጫግጫል። ጌታ ግን ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አይቶአልና። ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሀውንና ችግረኛውን ይጥሉ ዘንድ፥ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፥ ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር። በጻድቅ ዘንድ ያለው ጥቂት ነገር ከብዙ ክፉዎች ሀብት ይበልጣል። የክፉዎች ንድ ትሰበራለችና፥ ጌታ ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል። የንጹሓንን ቀኖች ጌታ ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘለዓለም ትሆናለች፥ በክፉ ዘመንም አያፍሩም፥ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። ክፉዎቸ ግን ይጠፋሉ፥ የጌታ ጠላቶች እንደ መስክ ውበት፥ እንደ ጢስም ተንነው ይጠፋሉ። ክፉ ይበደራል አይከፍልምም፥ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም። እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፥ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ። መንገዱን በወደደ ጊዜ፥ የሰው አካሄድ በጌታ ይጸናል። ቢወድቅም አይጣልም፥ ጌታ እጁን ይዞ ይደግፈዋልና። ጐለመስሁ አረጀሁም፥ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፥ ዘሩም በበረከት ይኖራል። ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፥ ለዘለዓለምም ትኖራለህ። ጌታ ፍርድን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፥ ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፥ የክፉዎች ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርሷም ለዘለዓለም ይኖራሉ። የጻድቅ አፍ ጥበብን ያናገራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}