በፍጹም ልቤ ጮኽሁ፥ አቤቱ፥ ስማኝ፥ ሥርዓትህን እፈልጋለሁ። ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አድነኝ፥ ምስክርህንም እጠብቃለሁ። ማለዳ ጮኽሁ፥ ቃልህንም ተስፋ አድርጌአለሁ። ቃልህን አስብ ዘንድ ዐይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ። አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ ድምፄን ስማ፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። በዓመፃ የሚያሳድዱኝ ቀረቡ፥ ከሕግህም ራቁ። አቤቱ፥ አንተ ቅርብ ነህ፥ መንገዶችህም ሁሉ ቅኖች ናቸው። ከዘለዓለም እንደ መሠረትኸው ከቀድሞ ጀምሮ ከምስክርህ የተነሣ አወቅሁ። ሕግህን አልረሳሁምና ችግሬን ተመልከት አድነኝም። ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፥ ስለ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መድኃኒት ከኀጥኣን ሩቅ ነው፥ ሥርዓትህን አልፈለጉምና። አቤቱ፥ ቸርነትህ እጅግ ብዙ ነው፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፥ ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልሁም። ቃልህን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ። ትእዛዝህን እንደ ወደድሁ ተመልከት፥ አቤቱ፥ በምሕረትህ ሕያው አድርገኝ። የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥ የጽድቅህም ፍርድ ሁሉ ለዘለዓለም ነው።
መዝሙረ ዳዊት 119 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙረ ዳዊት 119:145-160
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos