የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙረ ዳዊት 107:23-43

መዝሙረ ዳዊት 107:23-43 መቅካእኤ

በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላላቅ ውኆች ሥራቸውን የሚሠሩ፥ እነርሱ የጌታን ሥራ፥ በታላቅ አዘቅትም ያሉትን ድንቅ ሥራዎች አዩ። ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገዶችንም አስነሣ። ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፥ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች። ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። ዐውሎ ነፋሱን አስቆመ፥ ሞገዱም ጸጥ አለ። ዝም ብለዋልና ደስ አላቸው፥ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው። ስለ ጽኑ ፍቅሩ፥ ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ጌታን ያመስግኑ። በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት። ወንዞችን ምድረ በዳ፥ የውኃውንም ምንጮች ደረቅ መሬት አደረገው፥ ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት። ምድረ በዳን ወደ ውኃ ማጠራቀምያ፥ ደረቁንም ምድር ወደ ውኃ ምንጭነት ቀየረ። በዚያም ረሀብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ። እርሻዎችንም ዘሩ፥ ወይኖችንም ተከሉ፥ ፍሬንም ሰበሰቡ። ባረካቸውም እጅግም በዙ፥ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም። እነርሱ በጭቈና፥ በስቃይና በኃዘን ተዋርደው እያነሱ ሄዱ፥ በመኰንኖችም ላይ ውርደትን ዘረገፈ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አንከራተታቸው። ችግረኛንም ከመከራው አወጣው፥ ቤተሰቦችን እንደ በጎች መንጋ አበዛ። ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፥ ክፋት በሙሉ አፉን ይዘጋል። ጠቢብ ማነው? ይህንን ይፈጽም፥ እርሱ የጌታንም ጽኑ ፍቅር ይገነዘባል።