ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:19-30

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:19-30 መቅካእኤ

ነገር ግን ስለ እናንተ ባወቅሁ ጊዜ ደስ ተሰኝቼ እንድበረታታ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ እኔ ሆኖ ስለ ደኅንነታችሁ በቅንነት የሚጨነቅ እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝምና፤ የተቀሩት ሁሉ ግን የክርስቶስ ኢየሱስን ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም የሚሹ ናቸውና። ነገር ግን ጢሞቴዎስ ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል በማገልገል መፈተኑን ታውቃላችሁ። እንግዲህ በእኔ ዘንድ ያለውን ሁኔታ አይቼ፥ እርሱን ቶሎ እንደምልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እኔም ራሴ ደግሞ ፈጥኜ እንደምመጣ በጌታ ታምኜአለሁ። ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛና ወታደር፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን ኤጳፍሮዲጡስን ወደ እናንተ መላክ ፍጹም አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ሁላችሁን ይናፍቃልና፤ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል። በእርግጥ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ያደረገው ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ደግሞ ነው። እንግዲህ እንደገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በተቻለ ፍጥነት ወደ እናንተ እልከዋለሁ። እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፤ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ ምክንያቱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለመፈጸም ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ለክርስተቶስ ሥራ ሲል ለሞት ተቃርቦ ነበርና።