የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 29

29
መለከቶች የሚነፉበት የበዓል ቁርባን
1በሰባተኛውም ወር ከወሩ በመጀመሪያ ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ መለከቶች የሚነፉበት ቀን ነው። 2ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ 3እንዲሁም ደግሞ ለእህል ቁርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 4ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ። 5ማስተስረያም እንዲሆንላችሁ አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። 6በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ከመጠጡም ቁርባን ሌላ፥ እንደ ሕጋቸው ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው።
የማስተስረያ ቀን ቁርባን
7 # ዘሌ. 16፥29-34። በዚህም በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም አዋርዱ፤ ምንም ዓይነት ሥራ አትሥሩ። 8ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ። 9ለእህል ቁርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአንድ አውራ በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 10ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ፤ 11እንዲሁም ከሚያስተሰርየው ከኃጢአት መሥዋዕት፥ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ከመጠጥ ቁርባናቸውም ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።።
የዳስ በዓል ቁርባን
12 # ዘሌ. 23፥34፤ ዘዳ. 16፥13-15። በሰባተኛውም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፥ ሰባት ቀንም ለጌታ በዓል አድርጋችሁ ታከብራላችሁ። 13ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ዐሥራ ሦስት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ። 14ለእህል ቁርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለዐሥራ ሦስት ወይፈኖች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 15ለዐሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ፤ 16ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።
17በሁለተኛውም ቀን ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችን፥ ሁለት አውራ በጎችን፥ ነውር የሌለባቸው ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶችን፥ 18ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ 19ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባናቸው ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።
20“በሦስተኛውም ቀን ዐሥራ አንድ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 21ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ 22ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። 23በአራተኛውም ቀን ዐሥር ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 24ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸውም መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ 25ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።
26“በአምስተኛውም ቀን ዘጠኝ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 27ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ 28ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።
29“በስድስተኛውም ቀን ስምንት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 30ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ 31ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።
32“በሰባተኛውም ቀን ሰባት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 33ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ 34ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።
35“በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 36ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 37ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ 38ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።
39“እነዚህንም፥ ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታመጡት ቁርባን ሌላ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእህልም ለመጠጥም ቁርባን፥ ለአንድነትም መሥዋዕታችሁ በበዓላችሁ ጊዜ ለጌታ አቅርቡ። 40ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ጌታ እርሱን ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ