ኦሪት ዘኍልቊ 21
21
የናሱ እባብ
1 #
ዘኍ. 33፥40። በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል መምጣቱን ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ጦርነት አደረገ ከእርሱም ምርኮ ማረከ። 2እስራኤልም ለጌታ እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፦ “እነዚህን ሕዝቦች ፈጽሞ አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ።” 3ጌታም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት።
4 #
ዘዳ. 2፥1። ከሖርም ተራራ የኤዶምያስን ምድር በዙርያው አድርገው ለመሄድ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ ሕዝቡም በመንገድ እየተጓዙ ሳሉ ጉልበታቸው ደከመ። 5#1ቆሮ. 10፥9።ሕዝቡም በጌታና በሙሴ ላይ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብጽ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃም የለም፤ ሰውነታችንም ይህን የሚያንገሸግሽ እንጀራ ተጸየፈ።” 6ጌታም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ላከ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ። 7ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው እንዲህ አሉት፦ “በጌታና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን ኃጢአት ሠርተናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ ጌታ ጸልይልን።” ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። 8ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እባብን ሠርተህ በእንጨት ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያየው በሕይወት ይኖራል።” 9#2ነገ. 18፥4፤ ዮሐ. 3፥14።ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በእንጨት ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።
ጉዞ ወደ ሞዓብ
10የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኦቦትም ሰፈሩ። 11ከኦቦትም ተጉዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል፥ በዒዬዓባሪም ሰፈሩ። 12ከዚያም ተጉዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። 13ከዚያም ተጉዘው ከአሞራውያን ዳርቻ ትይዩ በተዘረጋው ምድረ በዳ ውስጥ በአርኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና። 14ስለዚህ በጌታ የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ፦
“ዋሄብ በሱፋ፥
የአርኖንም ሸለቆች፥
15እስከ ዔር ማደሪያ የተዘረጋው
በሞዓብም ዳርቻ የሚገኘው
የሸለቆች ተዳፋት መሬት።”
16ከዚያም ወደ ብኤር ተጓዙ፤ ይኸውም ጌታ ሙሴን፦ “ሕዝቡን ሰብስብ ውኃንም እሰጣቸዋለሁ” ብሎ የተናገረለት ጉድጓድ ነው።
17በዚያም ጊዜ እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ፦
አንተ ምንጭ ሆይ! ፍለቅ፤ እናንተም ዘምሩለት፤
18በበትረ መንግሥት በከዘራቸውም
የሕዝብ አዛውንቶች የቈፈሩት፥
አለቆችም የማሱት ጉድጓድ።
እነርሱም ከምድረ በዳም ወደ መቴና ተጓዙ፤ 19ከዚያም በኋላ ከመቴናም ወደ ነሃሊኤል፥ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት ተጓዙ፥ 20ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሀ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ።
ንጉሥ ሴዎን መሸነፉ
21እስራኤልም እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን ላከ፦ 22“በምድርህ ላይ ልለፍ፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጉድጓድም ውኃን አንጠጣም፤ ግዛትህን አልፈን እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጐዳና እንሄዳለን።” 23ሴዎንም እስራኤል በምድሩ ላይ እንዳያልፍ ከለከለ፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፥ ወደ ያሀጽም መጣ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ። 24እስራኤልም በሰይፍ መታው፥ ምድሩንም ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅ እስከ አሞን ልጆች ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ የጸና ነበረ። 25እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ። 26ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ከእጁ ወስዶ ነበር። 27ስለዚህ ባለቅኔዎች እንዲህ ብለው በምሳሌ ተቀኙ፦
“ወደ ሐሴቦን ኑ።
የሴዎን ከተማ ይሠራ፥ ይመሥረትም፤ 28#ኤር. 48፥45፤46።እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤
የሞዓብን ዔር፥ የአርኖንን ተራራ አለቆች በላ፤
29ሞዓብ ሆይ! ወዮልህ!
የካሞሽ ሕዝብ ሆይ! ጠፋህ፤
ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፥ ሴቶች ልጆቹንም ለምርኮ፥
ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ። 30ቀስትን ወረወርንባቸው፤ ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፉ፤
እሳቱ እስከ ሜድባ እስኪዛመት ድረስ ደመሰስናቸው።” 31እስራኤልም እንደዚህ በአሞራውያን ምድር ተቀመጡ። 32ሙሴም ኢያዜርን እንዲሰልሉ ሰላዮችን ላከ፤ መንደሮችዋንም ወሰዱ፥ በዚያም የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ።
ንጉሥ ዐግ መሸነፉ
33ተመልሰውም በበሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ እነርሱን ለመውጋት ወጣ። 34ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግኸው እንዲሁ ታደርግበታለህ።” 35ለእርሱም አንድ ሰው በሕይወት እንዳይተርፍ አድርገው እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ ገደሉ፤ ምድሩንም ወረሱ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቊ 21: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ