ኦሪት ዘኍልቊ 2
2
የአሰፋፈርና የጉዞ ቅደም ተከተል
1ጌታም ለሙሴና ለአሮን እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ 2“የእስራኤል ልጆች እያንዳንዱ በየዓላማው በየአባቶቻቸው ቤቶች ምልክት ይስፈሩ፤ በመገናኛው ድንኳን ትይዩ በሁሉም አቅጣጫ ይስፈሩ። 3በምሥራቅ በኩል ወደ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት እንደ ሠራዊቶቻቸው የይሁዳን ሰፈር ዓላማ የያዙት ይሆናሉ፤ የይሁዳ ልጆችም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ። 4ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 5በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የይሳኮር ነገድ ይሆናሉ፤ የይሳኮርም ልጆች አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ነበረ። 6ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ኀምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 7በእነርሱም አጠገብ የዛብሎን ነገድ ነበረ፤ የዛብሎንም ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበረ። 8ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ኀምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 9ከይሁዳ ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። እነዚህም አስቀድመው ይጓዛሉ።
10“በደቡብ በኩል በየሠራዊቶቻቸው የሮቤል ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የሮቤልም ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበረ። 11ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 12በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የስምዖን ነገድ ናቸው፤ የስምዖንም ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበረ። 13ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ኀምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 14ከእነርሱም ቀጥሎ የጋድ ነገድ ነበረ፤ የጋድም ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበረ። 15ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ኀምሳ ነበሩ። 16ከሮቤል ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ኀምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ ኀምሳ ነበሩ። እነርሱም ቀጥለው ይጓዛሉ።
17“ከዚያም በኋላ በሰፈሮቹም መካከል የመገናኛው ድንኳን ከሌዋውያን ሰፈር ጋር ይጓዛል፤ እንደ ሰፈራቸው እያንዳንዱ ሰው ስፍራቸውን ይዘው በየዓላሞቻቸው ይጓዛሉ።
18“በምዕራብ በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የኤፍሬም ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበረ። 19ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 20በእነርሱም አጠገብ የምናሴ ነገድ ነበረ፤ የምናሴም ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበረ። 21ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 22ከእነርሱም ቀጥሎ የብንያም ነገድ ነበረ፤ የብንያምም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበረ። 23ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 24ከኤፍሬም ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። እነርሱም ሦስተኛ ሆነው ይጓዛሉ።
25“በሰሜን በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የዳን ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የዳንም ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበረ። 26ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ስልሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 27በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የአሴር ነገድ ይሆናሉ፤ የአሴርም ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበረ። 28ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 29በእነርሱም አጠገብ የንፍታሌም ነገድ ነበረ፤ የንፍታሌምም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበረ። 30ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 31ከዳን ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ መቶ ኀምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። እነርሱም በየዓላሞቻቸው በመጨረሻ ይጓዛሉ።”
32ከእስራኤል ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ እነዚህ ናቸው፤ ከየሰፈሩ በየሠራዊቶቻቸው የተቈጠሩ ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ነበሩ። 33ሌዋውያን ግን ጌታ ሙሴን እንዳዘዘ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። 34የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ በዓላሞቻቸው አጠገብ ሰፈሩ፥ እንዲሁም በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች እየሆኑ ተጓዙ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቊ 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ