የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 2

2
የነህምያ ወደ ይሁዳ መላክ
1እንዲህም ሆነ በንጉሡ አርታሕሻስት በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር፥ የወይን ጠጅ በፊቱ ነበረ፥ የወይን ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ከዚህ ቀደም በፊቱ አዝኜ አላውቅም። 2ንጉሡም፦ “አልታመምክም ታዲያ ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኃዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም” አለኝ። እኔም እጅግ በጣም ፈራሁ። 3ንጉሡንም እንዲህ አልሁት፦ “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር! የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ስትፈርስ፥ በሮችዋም በእሳት ሲቃጠሉ ፊቴ ለምን አያዝን?” 4ንጉሡም፦ “ምን ትፈልጋልህ?” አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ። 5ንጉሡንም፦ “ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው፥ አገልጋይህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ መልሼ እንድሠራው የአባቶቼ መቃብር ወዳለበት ከተማ ወደ ይሁዳ እንድትልከኝ ነው” አልሁት። 6ንግሥቲቱ በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ፦ “መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ?” አለኝ። ንጉሡም ሊልከኝ ወደደ፤ እኔም ጊዜውን ወሰኜ ነገርኩት። 7ንጉሡን እንዲህ አልኩት፦ “ንጉሡ መልካም ፈቃዱ ቢሆን፥ ይሁዳ እስክደርስ ድረስ እንዲያሳልፉኝ ከወንዙ ማዶ ላሉት ገዢዎች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤ 8#ዕዝ. 7፥6።ለንጉሡ ደን ጠባቂ ለአሳፍ በቤቱ#2፥8 አንዳንድ ትርጉሞች “ቤተ መቅደሱ” ይሉታል። አጠገብ ላለው ምሽግ በሮች፥ ለከተማው ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይሰጠኝ” አልኩት። ንጉሡም በእኔ ላይ እንዳለችው እንደ አምላኬ መልካም እጅ#2፥8 አንዳንድ ትርጉሞች “የአምላኬ መልካም እጅ በእኔ ላይ ነበረችና” ብለው ይተረጉማሉ። ሰጠኝ።
9 # ዕዝ. 8፥22። በወንዙ ማዶ ወዳሉት ገዢዎች ሄጄ የንጉሡን ደብዳቤዎች ሰጠኋቸው። ንጉሡ ከእኔ ጋር የጦር አለቆችና ፈረሰኞች ልኮ ነበር። 10ሖሮናዊው ሳንባላጥና አገልጋይ የሆነው አሞናዊው ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደመጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ።
የነህምያ ግንቡን ተዘዋውሮ መመልከት
11 # ዕዝ. 8፥32። ኢየሩሳሌም ደረስሁ፥ በዚያም ሦስት ቀን ያህል ተቀመጥሁ። 12በሌሊት ተነሣሁ፥ እኔና ከእኔም ጋር ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ ነገር ግን አምላኬ ለኢየሩሳሌም እንዳደርገው በልቤ ያስቀመጠውን ነገር ለማንም አልተናገርኩም። ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም። 13በሌሊትም በሸለቆው በር ወጣሁ፥ ወደ “የዘንዶ ምንጭ” እና ወደ “የፍግ በር” ሄድኩ፤ የፈረሰውን የኢየሩሳሌምን ቅጥርና በእሳት የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትኩ። 14ወደ “የምንጭ በር” እና ወደ ንጉሡ መዋኛ አለፍኩ፤ ሆኖም ተቀምጬበት የነበረውን እንስሳ አያሳልፈውም ነበር። 15በሌሊት በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትኩ፤ ተመልሼም በሸለቆው በር ገባሁ፥ ከዚያም ተመለስኩ። 16ለአይሁድ ወይም ለካህናቱ ወይም ለታላላቆች ወይም ለሹማምቱ ወይም ሥራ ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች ስላልተናገርኩ፥ ሹማምንቱ ወዴት እንደ ሄድኩ ወይም ምን እንዳደረግሁ አላወቁም።
ቅጥሩን ለማደስ መወሰን
17እኔም፦ “ያለንበትን ችግር፥ ኢያሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ” አልኋቸው። 18#ዕዝ. 7፥6።መልካም የሆነችው የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ እንደሆነችና ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም፦ “እንነሣና እንሥራ” አሉ። ለመልካም ሥራ እጃቸውን አበረቱ። 19ሖሮናዊው ሳንባላጥ፥ አገልጋይ የሆነው አሞናዊው ጦብያና ዓረባዊው ጌሻም ይህንን ሰሙ፤ አፌዙብን፤ አንቋሸሹንም፤ “ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድነው? በንጉሡ ላይ እያመፃችሁ ነውን?” አሉ። 20እኔም፦ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም አገልጋዮቹ እንነሳለን፥ እንሠራለንም፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ድርሻ ወይም መብት ወይም መታሰቢያ የላችሁም” ብዬ መለስኩላቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ