የማርቆስ ወንጌል 6:6-19

የማርቆስ ወንጌል 6:6-19 መቅካእኤ

ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፥ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቆዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁና የማይሰማችሁ ከሆነ፥ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፥ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፥ “የዚህ ዓይነት ታምር በእርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎቹም፥ “ኤልያስ ነው” አሉ። አንዳንዶች ደግሞ፥ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፥ እኔ ራሱን ያስቆረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷአል አለ። ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፥ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። ዮሐንስ ሄሮድስን፥ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች