ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረዘይት ተራራ ወጡ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ” ከተነሣሁ በኋላ ግን፥ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ። ጴጥሮስም፥ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አላደርገውም” አለ። ኢየሱስም፥ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፥ “ከአንተ ጋር ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቆዩ” አላቸው። ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። ደግሞም፥ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ፥ ቢቻል ሰዓቱ ከእርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፥ “አባ፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየው። ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ መጥቷል።” ወዲያው እየተናገረ ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ አብረውትም ሰይፍና ዱላ የያዙ፥ ከካህናት አለቆች፥ ጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። አሳልፎ የሚሰጠውም፥ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷአቸው ነበር። እንደደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፥ “መምህር ሆይ” ብሎ ሳመው፤ ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት አሰሩትም። በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቆረጠ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቆመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን? በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።” በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተውት ሸሹ።
የማርቆስ ወንጌል 14 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 14
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 14:26-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች