የማርቆስ ወንጌል 14
14
የካህናት አለቆች ኢየሱስን ለመግደል እንደተማከሩ
(ማቴ. 26፥1-5፤ ሉቃ. 22፥1-2፤ ዮሐ. 11፥45-53)
1 #
ዘፀ. 12፥1-27። የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፥ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። 2ሆኖም፥ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር።
ኢየሱስን ሽቶ ስለቀባችው ሴት
(ማቴ. 26፥6-13፤ ዮሐ. 12፥1-8)
3 #
ሉቃ. 7፥37፤38። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፥ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አርከፈከፈችው። 4በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቆጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል? 5ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፥ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትዮዋንም ነቀፏት። 6ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፥ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች። 7#ዘዳ. 15፥11።ድኾች ምንም ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ 8እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች። 9እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።”
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት እንደተስማማ
(ማቴ. 26፥14-16፤ ሉቃ. 22፥3-6)
10ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። 11እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ነበር።
ኢየሱስ የፋሲካን እራት ከሐዋርያቱ ጋር እንደ በላ
(ማቴ. 26፥17-25፤ ሉቃ. 22፥7-14፤21-23፤ ዮሐ. 13፥21-30)
12የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፥ ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። 13እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ 14ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፥ መምህሩ፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?” ብሏል በሉት፤ 15እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን። 16ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ።
17በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። 18#መዝ. 41፥9።በማእድ ላይ ሳሉም፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከመካከላችሁ አንዱ፥ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። 19እነርሱም አዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፥ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። 20እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። 21የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት፤ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።”
የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት
(ማቴ. 26፥26-30፤ ሉቃ. 22፥14-20፤ 1ቆሮ. 11፥23-25)
22ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፥ “እንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው፤ 23ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። 24#ዘፀ. 24፥8፤ ኤር. 31፥31-34።ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ 25እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም።” 26ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረዘይት ተራራ ወጡ።
ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ መናገሩ
(ማቴ. 26፥31-35፤ ሉቃ. 22፥31-34፤ ዮሐ. 13፥36-38)
27 #
ዘካ. 13፥7። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ” 28#ማቴ. 28፥16።ከተነሣሁ በኋላ ግን፥ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ። 29ጴጥሮስም፥ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አላደርገውም” አለ። 30ኢየሱስም፥ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። 31ጴጥሮስም፥ “ከአንተ ጋር ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።
ኢየሱስ በጌቴሴማኒ እንደ ጸለየ
(ማቴ. 26፥36-46፤ ሉቃ. 22፥39-46)
32ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቆዩ” አላቸው። 33ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። 34ደግሞም፥ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። 35ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ፥ ቢቻል ሰዓቱ ከእርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፥ 36“አባ፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። 37ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ? 38ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” 39እንደገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየው። 40ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። 41ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። 42ተነሡ፤ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ መጥቷል።”
ይሁዳ ኢየሱስን እንደ አስያዘው
(ማቴ. 26፥47-56፤ ሉቃ. 22፥47-53፤ ዮሐ. 18፥3-12)
43ወዲያው እየተናገረ ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ አብረውትም ሰይፍና ዱላ የያዙ፥ ከካህናት አለቆች፥ ጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። 44አሳልፎ የሚሰጠውም፥ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷአቸው ነበር። 45እንደደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፥ “መምህር ሆይ” ብሎ ሳመው፤ 46ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት አሰሩትም። 47በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቆረጠ። 48ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቆመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን? 49#ሉቃ. 19፥47፤ 21፥37።በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።” 50በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተውት ሸሹ።
51ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ጣል ያደረገ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፥ 52በፍታውን ጥሎ ዕራቁቱን ሸሸ።
ኢየሱስ በአይሁድ ፍርድ ሸንጎ ፊት እንደ ቀረበ
(ማቴ. 26፥57-68፤ ሉቃ. 22፥54-55፤63-71፤ ዮሐ. 18፥13-14፤19-24)
53ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። 54ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፥ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር። 55የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። 56ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፥ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። 57አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ 58#ዮሐ. 2፥19።“ይህ፥ የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፥ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰምተነዋል።” 59ይህም ሆኖ፥ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። 60ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፥ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። 61ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደገና፥ የቡሩኩ ልጅ፥ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው። 62#ዳን. 7፥13።ኢየሱስም፥ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፥ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ። 63ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፥ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? 64#ዘሌ. 24፥16።ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?”፤ እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። 65በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፥ “እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።
ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደ ካደ
(ማቴ. 26፥69-75፤ ሉቃ. 22፥56-62፤ ዮሐ. 18፥15-18፤25-27)
66ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፥ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ 67ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኩር ብላ ተመለከተችውና፥ “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው። 68እርሱ ግን፥ “የምትዪውን አላውቅም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ። 69ገረዲቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፥ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደገና ተናገረች። 70እርሱ ግን አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፥ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፥ በእርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። 71እርሱ ግን፥ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር። 72ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስም፥ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ