ከዚያም በነገር እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛ ሰው መሆንህን እናውቃለን፤ የሰዎች ማንነት ስለማይገድህም አታዳላም፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም? እኛስ እንክፈል ወይስ አንክፈል?” ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ፥ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡልኝና ልየው” አላቸው። እነርሱም አመጡለት፥ “ይህ የማን መልክ ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የቄሣር ነው” አሉት። ኢየሱስም፥ “የቄሣርን ለቄሣር፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በእርሱ ተደነቁ። ከዚህ በኋላ የሙታን ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ የአንድ ሰው ወንድም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ይህ ሰው ሴትዮዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው አግብቷት ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሁለተኛውም ሴትዮዋን አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች። እንግዲህ፥ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሳኤ ለማናቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፥ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የምትስቱት እኮ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል ስለማታውቁ ነው፤ ሙታን ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። ስለ ሙታን ግን እንደሚነሡ እግዚአብሔር “እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤” እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቁጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ። ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፥ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፥ እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኋይልህ ውደድ።” ሁለተኛውም ይህ ነው፤ “ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።” ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም። ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፥ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም አእምሮህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኋይልህ መውደድ፥ እንዲሁም ጐረቤትህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፥ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፥ ጌታ ጌታዬን፥ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው፥ ይላል። “ታዲያ ዳዊት ራሱ ጌታ፥ ካለው፤ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?”። ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር። በሚያስተምርበትም ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ቀሚስ ለብሰው መዞርን ይወዳሉ፤ በየአደባባዩም የአክብሮት ሰላምታ ይሻሉ፤ በምኵራብ ከፍተኛውን ወንበር፥ በግብዣም ቦታ የከበሬታን ስፍራ ይፈልጋሉ፤ በረጅም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቁታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።” ኢየሱስ በገንዘብ ማስቀመጫው አንጻር ተቀምጦ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ገንዘብ ማስቀመጫ ሳጥን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤ አንዲት ድኻ መበለትም መጥታ ሁለት ሳንቲም የሚያክል የናስ ገንዘብ ጨመረች። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህቺ ድኻ መበለት ሳጥኑ ውስጥ ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ አስገባች። እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን በድህነት ዐቅሟ ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።”
የማርቆስ ወንጌል 12 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 12:13-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች