ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፥ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ፥ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘለዓለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቸር የለም፤ ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።” ሰውየውም፥ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላና፤ ተከተለኝም” አለው። ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ። ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፥ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል።” ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፥ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም አያቸውና፥ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው። ጴጥሮስም፥ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፥ ወንድሞችን፥ እኅቶችን፥ እናቶችን፥ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት የማይወርስ የለም።
የማርቆስ ወንጌል 10 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 10
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 10:17-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች