የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 10:13-31

የማርቆስ ወንጌል 10:13-31 መቅካእኤ

ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፥ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው። ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፥ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ፥ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘለዓለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቸር የለም፤ ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።” ሰውየውም፥ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላና፤ ተከተለኝም” አለው። ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ። ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፥ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል።” ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፥ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም አያቸውና፥ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው። ጴጥሮስም፥ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፥ ወንድሞችን፥ እኅቶችን፥ እናቶችን፥ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት የማይወርስ የለም። ነገር ግን ብዙዎች ፊተኞች የሆኑ ኋለኞች፥ ኋለኞች የሆኑም ፊተኞች ይሆናሉ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች