የማቴዎስ ወንጌል 5:22-42

የማቴዎስ ወንጌል 5:22-42 መቅካእኤ

እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወንድሙን የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙን ‘የማያስብ’ የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ‘ደደብ’ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። መባህን በመሠዊያው ላይ በምታቀርብበት ጊዜ፥ በዚያ ሳለህ ቅር የተሰኘብህ ወንድም እንዳለ ብታስታውስ፥ መባህን እዚያው በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ፤ አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ ከዚያ በኋላ መጥተህ መባህን አቅርብ። ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለሎሌው እንዳይሰጥህ ወደ እስር ቤት እንዳትገባ፤ ከባላጋራህ ጋር በመንገድ አብረኸው ስትሄድ ሳለህ ፈጥነህ ተስማማ፤ እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።” “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት አይቶ የተመኛት ሁሉ ከወዲሁ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዐይንህ ብታሰናክልህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ከአንተ ቆርጠህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። “‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት ጽሕፈት ይስጣት’ ተብሏል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። “ደግሞም ለቀደሙት ‘በውሸት አትማል ነገር ግን የማልኸውንም ለጌታ ስጥ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በፍጹም አትማሉ፤ በሰማይ አትማሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አትማሉ የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፤ አንዲቱን ጠጉር እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ስለዚህ ንግግራችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከእነዚህ የተረፈ ግን ከክፉው ነው። “‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉውን አትቃወሙት፤ ነገር ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ሊከስህ ፈልጎ እጀ ጠባብህን ሊወስድ የፈለገ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ እንድትሄድ ቢያስገድድህ፥ ሁለት ምዕራፍ ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚጠይቅህ ስጥ፤ ከአንተ ሊበደር ከሚፈልገው ፊትህን አታዙር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች