የማቴዎስ ወንጌል 27:1-31

የማቴዎስ ወንጌል 27:1-31 መቅካእኤ

በነጋም ጊዜ ሊቃነ ካህናትና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስን ሊገድሉት ተማከሩ፤ አስረውም ወሰዱት፤ ለገዢው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ብር ለሊቃነ ካህናቱና ለሽማግሌዎቹ መለሰላቸው፤ እንዲህም አለ “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ።” እነርሱ ግን “ታዲያ እኛ ምን አገባን? ጉዳዩ የራስህ ነው፤” አሉት። ብሩን በቤተ መቅደስ ጥሎ ወጣ፤ ሄዶም ታንቆ ሞተ። ሊቀ ካህናቱም ብሩን አንሥተው “የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አይፈቀድም” አሉ። ተማክረውም ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። በዚህም ምክንያት ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተብሎ ይጠራል። በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረው ተፈጸመ “ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ወሰዱ፤ ጌታም እንዳዘዘኝ ለሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉት።” ኢየሱስ በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ አልህ” አለው። በሊቃነ ካህናትና በሽማግሌዎች ሲከሰስ ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ “ስንት ነገር እንደሚመሰክሩብህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰለትም፤ በዚህም ገዢው እጅግ ተደነቀ። በዚያ በዓል፥ ገዢው ሕዝቡ የወደደውን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜ በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። ስለዚህ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ “ማንን ልፍታላችሁ ኢየሱስ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን?” አላቸው። በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ፥ ሚስቱ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ ጻድቅ ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት። ሊቃነ ካህናቱና ሽማግሌዎቹ ግን በርባን እንዲለቀቅ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፋ ሕዝቡን አግባቡ። ገዢውም መልሶ “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም “በርባንን” አሉ። ጲላጦስም “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው፤ ሁሉም “ይሰቀል!” አሉ። እርሱም “ምን ክፉ ነገር ሠራና?” አለ፤ እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ጲላጦስም ይህ ነገር ሁከት ከማስነሳት በስተቀር ምንም እንደማይጠቅም ባየ ጊዜ፥ ውሃ ወስዶ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ጉዳዩ የእናንተ ነው፤” ብሎ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት፤ ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ ሰበሰቡ። ልብሱንም ገፈው ቀይ ካባ አለበሱት፤ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፤ በፊቱም ተንበርክከው “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ አፌዙበት፤ ተፉበት፤ መቃውንም ነጥቀው ራሱን መቱት። ከአፌዙበትም በኋላ ካባውን ገፈው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች