የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 18:10-22

የማቴዎስ ወንጌል 18:10-22 መቅካእኤ

“ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና። የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ለማዳን ነው። “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ አይሄድምን? እውነት እላችኋለሁ፥ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል። እንደዚሁም ደግሞ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም። “ወንድምህ ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ገሥጸው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ታተርፈዋለህ፤ ባይሰማህ ግን አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር ቃል ነገር ሁሉ ይጸናልና፥ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ቁጠረው። እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱትም ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ በሚለምኑት በማንኛውም ነገር ሁሉ ቢስማሙ፥ በሰማያት ባለው አባቴ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው አለሁና።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ! ወንድሜ ስንት ጊዜ ቢበድለኝ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች