የማቴዎስ ወንጌል 18:1-10

የማቴዎስ ወንጌል 18:1-10 መቅካእኤ

በዚያች ሰዓት ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው? ብለው ጠየቁት። ሕፃን ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው አቆመው፤ እንዲህም አለ “እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንደዚህ ሕፃን ትሑት የሆነ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጠው እርሱ ነው። “እንደዚህ ሕፃን ያለውን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል። “ከማሰናከያው የተነሣ ዓለም ወዮላት፤ ማሰናከያ ግድ ይመጣልና፤ የማሰናከያ ማምጫ ምክንያት የሆነው ያ ሰው ግን ወዮለት! እጅህ ወይም እግርህ ካሰናከለህ ቆርጠህ ጣለው፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል፥ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዓይንህ ካሰናከለህ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፥ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃል። “ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች