ትንቢተ ሚልክያስ 3

3
የሚመጣው መልዕክተኛ
1 # ማቴ. 11፥10፤ ማር. 1፥2፤ ሉቃ. 1፥76፤ 7፥27። እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትደሰቱበትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
2 # ኢዩ. 2፥11፤ ራእ. 6፥17። እርሱ እንደ አንጥረኛ#3፥2 የሚያጠራ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና፤ የሚመጣበትን ቀን መቋቋም የሚችል ማን ነው? እርሱስ ሲገለጥ የሚቆም ማን ነው?
3ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቁርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ።
4በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቁርባን እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት ጌታን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።
5ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በአስማተኞች፥ በዘማውያን፥ በሐሰት በሚምሉ፥ የሠራተኛውን ደመወዝ በሚያስቀሩ፥ መበለቲቱንና#3፥5 ባሏ የሞተባት ሴት የሙት ልጅን በሚያስጨንቁ፥ ስደተኛውን በሚገፉ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
6 # ሲራ. 48፥10። እኔ ጌታ አልለወጥምና፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ አልጠፋችሁም።
7ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዜ ርቃችኋል፥ አልጠበቃችሁትምም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። እናንተ ግን፦ የምንመለሰው እንዴት ነው? ብላችኋል።
እግዚአብሔርን አትዝረፉ
8ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን ሰርቃችሁኛል። እናንተም፦ እንዴት እንሰርቅሃለን? ብላችኋል። በአሥራትና በቁርባን ነው።
9እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ ሰርቃችሁኛልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ።
10 # ዘሌ. 27፥30፤ ዘኍ. 18፥21-24፤ ዘዳ. 12፥6፤ 14፥22-29፤ ነህ. 13፥12። በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አስገቡ፤ የሰማያቶችን መስኮቶች ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
11ስለ እናንተ በላተኛውን እገሥጻለሁ፥ የአፈራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁ ያለውንም ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
12ሕዝቦች ሁሉ የተባረኩ ብለው ይጠሩአችኋል፥ የደስታ ምድር ትሆናላችሁና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
13በእኔ ላይ የድፍረት ቃላትን ተናግራችኋል፥ ይላል ጌታ። እናንተ ግን፦ በአንተ ላይ የተናገርነው ምንድነው? ትላላችሁ።
14እናንተም እንዲህ ብላችኋል፦ እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙን መጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ ፊት ኀዘንተኞች ሆነን መሄድ ምን ይጠቅመናል?
15አሁንም ትዕቢተኞችን የተባረኩ ብለን እንጠራቸዋለን፤ ክፉንም የሚሠሩ ታንጸዋል፥ እግዚአብሔርንም ይፈታተናሉ፥ ያመልጣሉም።
የታማኝ ሰው ሽልማት
16በዚያን ጊዜ ጌታን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ ጌታም አደመጠ፥ ሰማም፥ ጌታን ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያከብሩ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።
17እነርሱ የእኔ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ እኔ በምሠራበት ቀን፥ ሰው የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ።
18ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፥ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት ታያላችሁ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ