የሉቃስ ወንጌል 6:20-49

የሉቃስ ወንጌል 6:20-49 መቅካእኤ

እርሱም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዐይኑን አነሣ፤ እንዲህም አለ፦ “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።” እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁና ሲነቅፉአችሁ፥ በክፉም ስማችሁን ሲያጠፉ ብፁዓን ናችሁ! እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፤ በዚያን ቀን ተደሰቱ፤ በደስታም ዝለሉ፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ! መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ! ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ! ታዝናላችሁ እንባንም ታፈሳላችሁና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉ ነበርና። “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፤ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፤ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ ስጠው፤ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን እንኳ አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህንም የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። እንዲሁም ሰዎች ለእናንተ እንዲያደርጉላችሁ የምትወድዱትን ነገር እናንተ ለእነርሱ እንዲሁ አድርጉላቸው። “የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ ያን ያደርጋሉና። ልትቀበሉአቸው ተስፋ የምታደርጉአቸውን ሰዎች ብታበድሩ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ ባበደሩት ዋጋ ልክ እንዲመለስላቸው ለኀጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም አድርጉ፤ ይመለስልናልም ብላችሁ ምንም ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ። “አትፍረዱ እንዳይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ እንዳትኰነኑም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ፤ ስጡ ይሰጣችኋልም፤ በመልካምም መስፈሪያ የተጠቀጠቀና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና።” እርሱም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ዐይነ ስውር ዐይነ ስውርን መምራት ይችላልን? ሁለቱም በጉድጓድ አይወድቁምን? ደቀመዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። በወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትም? አንተ ራስህ በዐይንህ ያለውን ምሰሶ ሳታይ እንዴት ወንድምህን፦ ‘ወንድሜ ሆይ! በዐይንህ ያለውን ጉድፍ እዳወጣ ፍቀድልኝ፤’ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።” መልካም ዛፍ የተበላሸ ፍሬ አያፈራምና፤ እንዲሁም የተበላሸ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፤ ከአጣጥ ቁጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። መልካም ሰው በልቡ ከሚገኘው መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሚገኘው ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል፤ በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና። ስለምን “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ትሉኛላችሁ? የምለውን ግን አታደርጉም? ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ፥ ቃሎቼንም ሰምቶ የሚያደርጋቸው ሰው ማንን እንደሚመስል አሳያችኋለሁ፤ እርሱም፦ ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ፥ በዐለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፤ ደኅና ተደርጎም ስለ ታነጸ ሊያናውጠው አልቻለም። ነገር ግን ሰምቶ የማያደርገው ቤቱን ያለ መሠረት በምድር ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው፤ ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።”