የሉቃስ ወንጌል 5:16-32

የሉቃስ ወንጌል 5:16-32 መቅካእኤ

እርሱ ግን ገለል ብሎ ወደ በምድረ በዳዎች እየሄደ ይጸልይ ነበር። እንዲህም ሆነ፤ አንድ ቀን ሲያስተምር ሳለ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ ከኢየሩሳሌምም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ የሚፈውስበትም የጌታ ኃይል ከእርሱ ጋር ነበረ። እነሆም፥ አንድ መንቀሳቀስ የማይችል ሰው በአልጋ ተሸክመው አመጡ፤ አስገብተውትም በፊቱ ሊያኖሩት ይፈልጉ ነበር። ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ እርሱን ለማስገባት ምንም ዓይነት መንገድ ባለማግኘታቸው ወደ ሰገነቱ ወጡ፤ የጣራውንም ጡብ አሳልፈው በመካከላቸው ከነአልጋው በኢየሱስ ፊት አወረዱት። እምነታቸውንም አይቶ እንዲህ አለ፦ “አንተ ሰው! ኀጢአቶችህ ተሰረዩልህ።” ጻፎችና ፈሪሳውያንም፦ “ስድብን የሚሰነዝር ይህ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ ማን ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ይችላል?” እያሉ ያስቡ ነበር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ባወቀ ጊዜ መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “በልባችሁ ምን እያሰባችሁ ነው? ‘ኀጢአቶችህ ተሰረዩልህ፤’ ከማለትና ‘ተነሣና ሂድ፤’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” ብሎ፥ መንቀሳቅስ የተሳነውን ሰው፦ “እነሆ አዝሃለሁ፤ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። ወዲያውኑ በፊታቸው ተነሣ፤ ተኝቶበትም የነበረውን ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። ሁሉም ተገረሙ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ በፍርሃትም ተሞልተው፦ “ዛሬስ አስደናቂ ነገሮችን አየን፤” አሉ። ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ በመቅረጫው ስፍራ ተቀምጦ ተመለከተና፦ “ተከተለኝ፤” አለው። እርሱም ሁሉንም ነገር ትቶ፤ ተነሥቶ ተከተለው። ሌዊም ታላቅ ግብዣ በቤቱ አደረገለት፤ ከቀራጮችና ከሌሎችም ብዙ ሕዝብ በማዕድ ከእነርሱ ጋር ተቀምጠው ነበር። ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም፦ “ስለምን ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ? ትጠጣላችሁም?” ብለው በደቀ መዛሙርቱ ላይ አጉረመረሙ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ ኀጢአተኞችን ወደ ንስሓ ልጠራ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።”