የሉቃስ ወንጌል 22:29-46

የሉቃስ ወንጌል 22:29-46 መቅካእኤ

አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ ለመንግሥት እሾማችኋላሁ፤ በመንግሥቴም ከእኔ ማዕድ ትበላላአችሁ፥ እንዲሁም ትጠጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይም ለመፍረድ በዙፋኖች ላይ ትቀመጣላችሁ። ጌታም “ስምዖን ስምዖን ሆይ! እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና፤” አለ። እርሱም “ጌታ ሆይ! ወደ ወኅኒም ሆነ ወደ ሞት ከአንተ ጋር ለመሄድ ዝግጁ ነኝ፤” አለው። እርሱ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፥ ‘አላውቅህም’ እያልህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው። ከዚያም፥ “ያለ ቦርሳና ያለ ከረጢት፥ ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም” አሉ። እርሱም “አሁን ግን ቦርሳ ያለው ይያዘው፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። ይህ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ የግድ መፈጸም አለበት እላችኋልለሁ፤ አዎን፤ ስለ እኔ የተባለው አሁን ይፈጸማልና፤” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ፤” አሉት። እርሱም “ይበቃል፤” አላቸው። እንደ ለመደው ወጥቶም ወደ ደብረዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ ተከተሉት። ወደ ስፍራውም ደርሶ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ፤” አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፤ ተንበርክኮም፦ “አባት ሆይ! ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን፤ የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ፤” እያለ ይጸልይ ነበር። ከሰማይም የሚያበረታው መልአክ ታየው። በስቃይ ጣር ውስጥ ሆኖ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም ወደ መሬት እንደሚንጠባጠቡ የደም ጠብታዎች ሆኑ። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ፤” አላቸው።