የሉቃስ ወንጌል 21:5-24

የሉቃስ ወንጌል 21:5-24 መቅካእኤ

አንዳንዶቹም ስለ ቤተ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ “ይህማ የምታዩት ሁሉ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል፤” አለ። እነርሱም “መምህር ሆይ! እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሊሆን መቃረቡን የሚያሳየው ምልክቱ ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እንዲህም አለ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች ‘እኔ ነኝ፤ ዘመኑም ቀርቦአል፤’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ። ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም።” በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይታያል። ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ጭነው ይይዟችኋል፤ ያሳድዱአችኋ፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። ሰለዚህም የመከላከያ መልስ አስቀድሞ ማዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ። ተቃዋሚዎቻችሁ በሙሉ ሊቃወሙትና ሊከራከሩት የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። ወላጆችና ወንድሞች፥ ዘመዶችና ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ በሁሉም ከስሜ የተነሣ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ። “ኢየሩሳሌም ግን በሠራዊት ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በመካከልዋም ያሉ ከእርሷ ይራቁ፤ በገጠር ያሉም ወደ እርሷ አይግቡ፤ የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የቅጣት ጊዜ ነውና። በነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቁጣ ይሆናልና፤ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉ ይሰደዳሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።