በቅርብ እየተከታተሉትም ለገዢው ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። እነርሱም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት “መምህር ሆይ! እውነትን እንደምትናገርና እንደምታስተምር በሰው ፊትም እንደማታደላ እናውቃለን፤ ይልቁንም በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ፤ ለቄሣር ግብር እንድንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም?” አሉት። እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ መልኩና ጽሑፉ የማን ነው?” አላቸው። ሲመልሱም “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። በሕዝቡም ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ። የሙታንን ትንሣኤ የሚክዱ ሰዱቃውያን ቀርበው ጠየቁት፤ እንዲህም አሉ፤ “መምህር ሆይ! ሙሴ ‘አንድ ሰው ባለትዳር ወንድም ቢኖረውና፥ እርሱም ሳይወልድ ቢሞት፥ ወንድሙ የእርሱን ሚስት አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ፤’ ብሎ ጻፈልን። እንግዲህ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሁለተኛውም አገባት፤ ሦስተኛውም፤ ሰባተኛውም እንዲሁ፤ ልጅም ሳይተው ሞቱ። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። እንግዲህ ሰባቱ አግብተዋታልና ሴቲቱ በትንሣኤ ከእነርሱ ለማንኛቸው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፤ ለሚመጣው ዓለምና ለሙታን ትንሣኤ ተገቢ የሆኑት ግን አያገቡም፤ አይጋቡምም፤ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ወደ ፊት ሊሞቱም አይችሉም፤ የትንሣኤም ልጆች እንደመሆናቸው መጠን የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ሙታን እንደሚነሡ ግን ሙሴ እራሱ በቁጥቋጦው ታሪክ ጌታን ‘የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ’ በማለቱ አስታወቀ፤ ሁሉም ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው “መምህር ሆይ! መልካም ተናገርህ፤” አሉት። ከዚያም ወዲህ ምንም ሊጠይቁት አልደፈሩም። እንዲህም አላቸው፥ “መሢሕ የዳዊት ልጅ ነው” እንዴት ይላሉ? ዳዊትም ራሱ በመዝሙራት መጽሐፍ፦ “ጌታ ጌታዬን እንዲህ አለው፦ በቀኜ ተቀመጥ፥ ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስካደርግልህ ድረስ” ይላልና፤ እንግዲህ ዳዊት እራሱ “ጌታ ብሎ ይጠራዋል፤ ታዲያ እንዴት ልጁ ይሆናል?” ሕዝቡም ሁሉ እየሰሙት ደቀ መዛሙርቱን “ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠንቀቁ፤ የመበለቶችን ቤት የሚበሉ፥ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ ናቸው፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ፤” አለ።
የሉቃስ ወንጌል 20 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 20
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 20:20-47
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች