የሉቃስ ወንጌል 11:14-32

የሉቃስ ወንጌል 11:14-32 መቅካእኤ

መናገርም የተሳነውን ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣ በኋላ መናገር የተሳነው ሰው ተናገረ፥ ሕዝቡም ተደነቁ፤ ከእነርሱ ዘንድ አንዳንዶች ግን፦ “በብዔልዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል፤” አሉ። ሌሎችም ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሱ የተለያየ መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል። ሰይጣንም ደግሞ እርስ በርሱ ቢለያይ መንግሥቱ እንዴት ይቆማል? እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል እንደማወጣ እናንተ ብላችኋልና፤ እኔስ በብዔልዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ፥ ልጆቻችሁ በማን ያስወጣሉ? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥቷል። በማናቸውም ጊዜ ኀይለኛ ሰው በሚገባ የጦር ዕቃውን ታጥቆ የራሱን ግቢ ቢጠብቅ፥ ያለው ንብረቱ በሰላም የተጠበቀ ይሆናል፤ ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ አደጋ ጥሎበት ካሸነፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን የጦር ዕውቃን ይወስድበታል፤ ምርኮውንም ያካፍላል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋርም የማይሰበስብ ይበትናል። “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍትን ፈልጎ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ ባለማግኘቱ ግን፦ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ፤’ ይላል፤ ሲመጣም ተጠርጎና ተስተካክሎ ያገኘዋል። በዚያም ጊዜ ሄዶ ከእርሱ የባሱ ክፉ ሌሎች ሰባት መናፍስትን ከእርሱ ጋር ያመጣል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ የዚያም ሰው ሁኔታ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ይሆናል።” ኢየሱስም ይህንን በመናገር ላይ ሳለ፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፦ “የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው፤” አለችው። እርሱ ግን፦ “በእርግጥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው፤” አለ። ሕዝብም በብዛት እየተሰበሰቡ በነበሩ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር፦ “ይህ ትውልድ ክፉ ትውልድ ነው፤ ምልክትን ይፈልጋል፤ ከዮናስም ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ትነሳለች፥ በእነርሱም ላይ ትፈርዳለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ በዚህ አለ። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ይነሳሉ፥ በእርሱም ላይ ይፈርዳሉ፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ በዚህ አለ።