የሉቃስ ወንጌል 1:42-53

የሉቃስ ወንጌል 1:42-53 መቅካእኤ

በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣትዋ እንዴት ያለ ነገር ነው? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ ወደ ጆሮዬ በደረሰ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸም ያመነች ምንኛ ብፅዕት ናት።” ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ እኔን ዝቅተኛይቱን አገልጋይ ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ሁሉን የሚችል እርሱ ለእኔ ታላላቅ ነገሮችን አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ በሚፈሩት ላይ ይኖራል። በክንዱ ኃያል ሥራን ሠርቶአል፤ በልባቸው የሚታበዩትን በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ሀብታሞችን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።