መጽሐፈ ኢዮብ መግቢያ

መግቢያ
መጽሐፈ ኢዮብ ከጥበብ መጻሕፍት አንዱ ሲሆን፥ የንጹሕ ሰው መሰቃየትን አስመልክቶ የሚነሡትን ጥያቄዎች በትረካ የሚዳስስ ጽሑፍ ነው። በትውልዱ እስራኤላዊ ባልሆነው ኢዮብ ላይ የሚደርሰውን የፈተና መጀመርያ በመጀመርያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ እናነባለን። የዚህ ሁሉ መነሻ በእግዚአብሔርና የሰው ልጆች ተቀናቃኝ በሆነው በሰይጣን መካከል የተከናወነው ንግግር ነው። እግዚአብሔር በኢዮብ ጻድቅነት ሲደሰት፥ ሰይጣን ግን የኢዮብ እግዚአብሔርን መፍራት እውንተኛነት እንደሚጎድለውና በጥቅም ላይ እንደ ተመሠረተ በመቍጠር ይሟገታል። በሌላ አነጋጋር ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚያመልከውም ሆነ መልካም አኗኗር የሚከተለው ሀብትን፥ ጤናንና ጥቅምን ለማግኘት ብሎ እንጂ፥ በእውነት እግዚአብሔርን አፍቅሮ አይደለም እንደማለት ነው። እግዚአብሔርም የኢዮብ እውነተኛነት ይገለጥ ዘንድ ችግር እንዲገጥመው ይፈቅዳል።
የኢዮብ ሦስት ጓደኞች የደረሰበትን ሰምተው ሊያጽናኑት ይመጣሉ። ኢዮብ ብሶቱን መግለጽ ይጀምራል። ጓደኞቹ የኢዮብ መከራ የኃጢአት ቅጣት ነው ብለው ያስባሉ። ከኢዮብም ጋር በዚህ ሐሳብ ይከራከራሉ። ለነሱ መፍትሔው የሚመጣው ኢዮብ ኃጢአቱን አምኖ ንስሐ ሲገባ ነው። ኢዮብ ግን የጓደኞቹን ሐሳብ አይቀበልም። ይልቁንም እግዚአብሔር ለዚህ ጉዳይ መልስ እንዲሰጠው ደጋግሞ ይጠይቃል። በዚሁ አጋጣሚ ኤሊሁ የሚባል አንድ ወጣት የኢዮብን ጓደኞች የሚመስል ክርክር ያቀርባል። እንደ ጓደኞቹም ኢዮብን ይወቅሰዋል። በታሪኩ መጨረሻ እግዚአብሔር ለኢዮብ ይገለጻል። ነገር ግን ኢዮብ ወይም አንባቢ በሚጠብቀው መልክ እግዚአብሔር መልስ አይሰጥም። ኢዮብ፥ በታሪኩ መጀመርያ፥ በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል የነበረውን ክርክር አያውቅም። ሆኖም እግዚአብሔር ስለዚህ ጉዳይ ምንም አያነሣም፤ ኢዮብ ለምን እንደተሰቃየ አይናገርም። ይልቁንም እግዚአብሔር ከሰው ውጭ ስላሉ ፍጥረታት አስደናቂነት በመዘርዘር ያብራራል። እግዚአብሔር ንግግሩን ሲጨርስ ኢዮብ መገረሙን፥ አድናቆቱንና ትንሽነቱን ይመሰክራል። ምንም እንኳን ኢዮብ ቢያማርር፥ እግዚአብሔርን ግን አልተሳደበም። ከዚህ አንጻር የሰይጣን ግምት ውድቅ ሆኗል። “እንደ ኢዮብ የመሰለ ጻድቅ ሰው የለም” የሚለው የእግዚአብሔርም አቋም ትክክለኛነት ተረጋግጧል። በተጨማሪም የኢዮብ ግልጽነትና ንጹሕነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል። በዚህም እግዚአብሔር ኢዮብን ይደግፈዋል። እጥፍ ድርብ አድርጎ ሀብት፥ ጤናና ልጆችን ይሰጠዋል። ጓደኞቹን ግን ከመውቀስም አልፎ የኢዮብን መሥዋዕትና ጸሎት እንዲጠይቁ ያዛቸዋል።
የመጽሐፈ ኢዮብን ክፍሎች እንድሚከተለው ማቅረብ ይቻላል
1. መቅድም (1፥1—2፥13)
2. የመጀመርያ ዙር ንግግሮችና ክርክር (3፥1—14፥22)
3. የሁለተኛ ዙር ንግግሮችና ክርክር (15፥1—21፥34)
4. የሦስተኛ ዙር ንግግሮችና ክርክር (22፥1—27፥23)
5. ስለ ጥበብ የቀረበ ቅኔ (28፥1-28)
6. የኢዮብ መከራ (29፥1—31፥40)
7. የኤሊሁ ንግግር (32፥1—37፥24)
8. እግዚአብሔር ለኢዮብ ተገለጠ (38፥1—42፥6)
9. መደምደምያ (42፥7-17)
ምዕራፍ

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ