መጽሐፈ ኢዮብ 34
34
1ኤሊሁም ደግሞ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“እናንተ ጥበበኞች፥ ቃሌን ስሙ፥
እናንተም አዋቂዎች፥ ወደ እኔ አድምጡ።
3 #
ኢዮብ 12፥11። ምላስ መብልን እንደሚያጣጥም፥
ጆሮም ቃላትን ይለያልና።
4ፍትሕን እንምረጥ፥
መልካሙንም ነገር በመካከላችን እንወቅ።
5 #
ኢዮብ 33፥9-10። ኢዮብ፦ እኔ ንጹሕ ነኝ፥
እግዚአብሔር ግን ፍርድ ከለከለኝ፥
6 #
ኢዮብ 9፥20። ምንም እውነተኛ ብሆን እንደ ውሸተኛ ተቈጠርሁ፥
ምንም ባልበድል ቁስሌ የማይፈወስ ነው ብሏል።
7-9ኢዮብም፦ በእግዚአብሔር መደሰት
ለሰው ምንም አይጠቅምም ብሏልና፥
ከበደለኞች ጋር የሚተባበር፥
ክፉ ከሚያደርጉስ ጋር የሚሄድ፥
ሹፈትን እንደ ውኃ የሚጠጣት
እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?#ኢዮብ 9፥22-23፤30-31፤ 21፥15፤ 35፥3።”
10 #
ኢዮብ 36፥23። “ስለዚህ የምታስተውሉ ሰዎች፥ ስሙኝ፥
ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር፥
በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ።
11 #
መዝ. 62፥13፤ ምሳ. 24፥12፤ ማቴ. 16፥27፤ ሮሜ 2፥6፤ 2ቆሮ. 5፥10፤ ራእ. 22፥12። ለሰው እንደ ሥራው ይመልስለታል፥
ሰውም እንደ መንገዱ ያገኝ ዘንድ ያደርጋል።
12 #
ኢዮብ 8፥3። በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥
ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም።
13 #
ኢዮብ 38፥4-7። ምድርን አደራ የሰጠው ማን ነው?
ዓለምንስ ሁሉ በእርሱ ላይ ያኖረ ማን ነው?
14እርሱ ልቡን ወደ ራሱ ቢመልስ፥
መንፈሱንና እስትንፋሱን ወደ ራሱ ቢሰበስብ፥
15 #
ኢዮብ 10፥9። ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፥
ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል።”
16“አስተዋይ ከሆንክ ይህን ስማ፥
ንግግሬንም አድምጥ።
17በውኑ ጽድቅን የሚጠላ ሊገዛ ይገባዋልን?
ጻድቅና ኃያል የሆነውንስ በደለኛ ታደርገዋለህን?
18ማንም ሰው ንጉሡን፦ በደለኛ ነህ፥
መኰንኖቹን፦ ክፉዎች ናችሁ ይላልን?
19 #
ዘዳ. 10፥17፤ 2ዜ.መ. 19፥7፤ ጥበ. 6፥7፤ የሐዋ. 10፥34፤ ሮሜ 2፥11፤ ኤፌ. 6፥9፤ ቈላ. 3፥25፤ 1ጴጥ. 1፥17። እነርሱ ሁሉ የእጁ ሥራ ናቸውና
ለአለቆች አያደላም፥
ሀብታሙንም ሰው ከድሀው ይበልጥ አይመለከትም።
20 #
ኢዮብ 21፥13። እነርሱ በእኩለ ሌሊት በድንገት ይሞታሉ፥
ሕዝቡ ተንቀጥቅጦ ያልፋል፥
ኃያላንም ያለ ምንም ድካም ይወገዳሉ።
21ዐይኖቹ የሰውን መንገድ ይመለከታሉ፥
የሰውን እርምጃ በሙሉ ያያል።
22ክፋትን የሚሠሩ የሚደበቁበት
ጨለማ ወይም የሞት ጥላ የለም።
23ሰው ወደ እግዚአብሔር ለፍርድ ለመቅረብ
ቀጠሮ አይሰጠውም።
24 #
መዝ. 2፥9። ኃያላንን ያለ ምርመራ ይሰባብራል፥
በእነርሱም ፋንታ ሌሎችን ያቆማል።
25ሥራቸውን ያውቃል፥
በሌሊት ይገለባብጣቸዋል፤ እነርሱም ይደቃሉ።
26ሰዎች እያዩ እንደ ክፉዎች ይመታቸዋል፥
27-28የድሀውን ልቅሶ እስኪሰማ ድረስ፥
የችግረኛውን ድምፅ እስኪሰማ ድረስ፥
እርሱን ከመከተል ርቀዋልና፥
ከመንገዱም አንዱንም አልተመለከቱምና።
29ሕዝብንም ሆነ ሰውን በተመለከተ፥
ዝም ቢል የሚፈርድ ማን ነው?
ፊቱንስ ቢሰውር የሚያየው ማን ነው?
30ይህም እግዚአብሔርን የሚክድ እንዳይነግሥ፥
በሕዝቡም ላይ ወጥመድ የሚዘረጋ እንዳይኖር ነው።
31እግዚአብሔርን፦ እኔ ሳልበድል ቅጣት ተቀበልሁ፥
32የማላየውን ነገር አንተ አስተምረኝ፥
ኃጢአትንም ሠርቼ እንደሆነ፥
ደግሜ አልሠራም የሚለው ማን ነው?
33በውኑ አንተ ተቃውመኸዋልና
ሽልማቱ አንተ እንደምትወድደው ይሆናልን?
እኔ ሳልሆን አንተ ነህ የምትመርጠው፥
ስለዚህ የምታውቀውን ተናገር።
34የሚሰሙኝ ጥበበኞች ሁሉ፥
አስተዋዮችም እንዲህ ይሉኛል፦
35 #
ኢዮብ 35፥16፤ 38፥2፤ 42፥3። ኢዮብ ያለ እውቀት ተናግሮአል፥
ንግግሩም ማስተዋል ይጎድለዋል።
36ኢዮብ እስከ መጨረሻ ድረስ ምነው በተፈተነ ኖሮ!
እርሱ እንደ ክፉዎች መልሶአልና፥
37በኃጢአቱም ላይ ዓመፅን ጨምሮአልና፥
በእኛም መካከል በፌዝ ያጨበጭባልና፥
እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ቃላትን ያበዛልና።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 34: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ