መጽሐፈ ኢዮብ 31

31
1“ከዐይኖቼ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ፥
እንግዲህ ቈንጆይቱን እንዴት በፍትወት እመለከታለሁ?
2የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ከላይ፥
ሁሉንም የሚችል አምላክ ርስትስ ከአርያም ምንድነው?
3መዓትስ ለኃጢአተኛ፥
መገለልስ ለሚበድሉ ሰዎች አይደለችምን?
4መንገዴን አያይምን?
እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?”
5-6“በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥
እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ።
በሐሰት ሄጄ እንደሆነ
እግሬም ለሽንገላ ቸኩላ እንደሆነ፥
7እርምጃዬ ከመንገድ ወጥቶ፥
ልቤም ዓይኔን ተከትሎ፥
ነውርም ነገር ከእጄ ጋር ተጣብቆ እንደሆነ፥
8እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፥
የሚበቅለውም ሁሉ ይነቀል።”
9“ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደሆነ፥
በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደሆነ፥
10ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥
ሌሎችም በእርሷ ላይ ይጐንበሱ።
11ይህ ክፉ አበሳ፥
ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፥
12ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥
ቡቃያዬንም ሁሉ የሚያቃጥል ነውና።”
13“ወንዶችና ሴቶት አገልጋዮቼ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥
ሙግታቸውን ንቄ እንደሆነ፥
14እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ?
በጐበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታልሁ?
15እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን?
በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለንምን?”
16 # ጦቢ. 4፥7-11፤16። “ድሀውን ከሚያስፈልገው ከልክዬ፥
የመበለቲቱን ዐይን አጨልሜ እንደሆነ፥
17እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደሆነ፥
ወላጅ አልባውም ሳይደርሰው ቀርቶ እንደሆነ፥
18ለነገሩማ ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባት ሆኜ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥
መበለቲቱንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፥
19ከልብስ እጦት የተነሣ አንድ ሰው ሲጠፋ አይቼ፥
ወይም ድሀ የሚሸፈንበት ሲያጣ ተመልክቼ፥
20ማን ነው ከአንጀቱ ያልባረከኝ፥
በበጎቼም ጠጉር ያልሞቀ?
21በይፋ ድጋፍ አለኝ ብዬ፥
በወላጅ አልባ ላይ እጄን አንሥቼ የቃታሁ እንደሆነ፥
22ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፥
ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር።
23የእግዚአብሔር መዓት አስደንግጦኛልና፥
በክብሩም ፊት ምንም ለማድረግ አልቻልሁም።”
24 # ሲራ. 31፥5-10። “ወርቅን ተስፋ አድርጌ፥
ንጹሑንም ወርቅም መተማመኛዬ ብዬ ጠርቼው እንደሆነ፥
25ሀብቴ ስለ በዛ፥
እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደሆነ፥
26ፀሐይ ስታበራ
ጨረቃም በክብር ስትሄድ አይቼ፥
27ልቤ በስውር ተታልሎ፥
አፌም እጄን ስሞ እንደሆነ፥ #31፥27 ፀሐይንና ጨረቃን አምልኬ እንደሆነ።
28ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና፥
ይህ ደግሞ በፈራጆች የሚያስቀጣ በደል በሆነ ነበር።”
29“በሚጠላኝ መጥፋት ደስ ብሎኝ
ክፉ ነገርም ባገኘው ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደሆነ፥
30ነገር ግን ነፍሱ እንዲጠፋ በመራገም
አንደበቴ ኃጢአት እንዲሠራ አልፈቀድሁም፥
31በድንኳኔ ሥር የሚኖሩ ሰዎች፦
‘በሥጋ ያልጠገበ ማን ይገኛል?’ ይሉ የለምን?
32እንግዳው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥
ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር፥
33በደሌንም በውስጤ በመሸሸግ
ኃጢአቴን እንደ ሰው ሰውሬ እንደሆነ፥
34ከሕዝብ ብዛት የተነሣ ፈርቼ፥
የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥
ዝም ብዬ ከደጅ ያልወጣሁ እንደሆነ፥
35የሚያዳምጠኝ ምነው በኖረልኝ!
እነሆ የእጄ ምልክት፥
ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፥
ከባላጋራዬ የተጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ!
36በትከሻዬ ላይ እሸከመው፥
አክሊልም አድርጌ በራሴ ላይ አስረው ነበር፥
37የእርምጃዬን ቍጥር አስታውቀው፥
እንደ መስፍንም ሆኜ እቀርብለት ነበር።”
38“እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኾ እንደሆነ፥
ትልሞቹም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደሆነ፥ #31፥38 “ግፍ ሠርተሀል ብለው የተቆጡ እንደሆነ”፤ ምሳሌያዊ ንግግር ነው።
39ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፥
የባለቤቶችንም ነፍስ አሳዝኜ እንደሆነ፥
40በስንዴ ፋንታ አሜከላ፥
በገብስም ፋንታ ኩርንችት ይውጣብኝ።” የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ