የዮሐንስ ወንጌል 4:43-53

የዮሐንስ ወንጌል 4:43-53 መቅካእኤ

ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች፥ እራሳቸውም ለበዓል መጥተው ነበርና፥ በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደመጣ ሰምቶ፥ ልጁ ሊሞት ስለ ቀረበ፥ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። ስለዚህም ኢየሱስ “ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም፤” አለው። ሹሙም “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ፤” አለው። ኢየሱስም “ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ፤” አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። እርሱም ሲወርድ ሳለ አገልጋዮቹ ተገናኙትና “ብላቴናህ በሕይወት አለ፤” ብለው ነገሩት። እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ትናንት በሰባት ሰዓት ትኩሳቱ ለቀቀው፤” አሉት። አባቱም፥ ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት አለ፤” ባለው በዚያ ሰዓት እንደሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋር አመነ።