መስቀሉንም ተሸክሞ የራስ ቅል ወደሚሉት ስፍራ፥ በዕብራይስጥም ጎልጎታ ወደ ተባለው ቦታ ወጣ። በዚያም ሰቀሉት፤ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሁለት፥ አንዱን በአንድ ጎን፥ አንዱን በሌላ ጎን፥ ኢየሱስንም በመካከላቸው አድርገው ሰቀሉ። ጲላጦስም ደግሞ ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ ጽሕፈቱም “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበረ። ኢየሱስም የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ነበረና ከአይሁድ ብዙዎች ይህን ጽሕፈት አነበቡት፤ በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ተጽፎ ነበር። ስለዚህ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን “እርሱ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ አለ ብለህ ጻፍ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ፤” አሉት። ጲላጦስም “የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” ብሎ መለሰ። ወታደሮቹም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ወታደር አንድ ክፍል እንዲደርስ በአራት ከፋፈሉአቸው፤ እጀ ጠባቡንም እንዲሁ ወሰዱ። እጀ ጠባቡ ግን ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። ስለዚህም እርስ በርሳቸው “ለማን እንዲሆን ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም “ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነበር። ወታደሮቹም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም እንዲሁም መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር። ኢየሱስም እናቱንና ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን “አንቺ ሴት ሆይ! እነሆ ልጅሽ” አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን “እናትህ እነኋት” አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከወዲሁ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉም ቃል ይፈጸም ዘንድ “ተጠማሁ” አለ። በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት። ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።
የዮሐንስ ወንጌል 19 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 19
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 19:17-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች