የዮሐንስ ወንጌል 13:1-20

የዮሐንስ ወንጌል 13:1-20 መቅካእኤ

ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን፥ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው። እራትም ሲበሉ፥ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካስገባ በኋላ፥ ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደሰጠው፥ ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣና ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ አውቆ፥ ከማእድ ተነሣ፤ ልብሱንም አኖረ፤ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውሃ ጨመረ፤ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ማጠብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ማበስ ጀመረ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም “የእኔን እግር በጭራሽ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም “ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ድርሻ የለህም፤” ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን፥ እጄንና ራሴንም ጭምር” አለው። ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም አይደላችሁም፤” አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና “ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም” አለው። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ ስለሆንኩም መልካም ትናገራላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተም እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህንን ስታውቁና ስታደርጉ ብፁዓን ናችሁ። ስለ ሁላችሁም አይደለም የምናገረው፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። አሁን አስቀድሜ የምነግራችሁ፥ በተከሠተ ጊዜ እኔ መሆኔን ታምኑ ዘንድ ነው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን ማንኛውንም ሰው የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።”