አንድ ሰው ታሞ ነበር፤ እርሱም እንደ ማርያምና እንደ እኅትዋ ማርታ ከቢታንያ የነበረው አልዓዛር ነው። ማርያም ጌታን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጉርዋ ያበሰችው ስትሆን፤ የታመመውም አልዓዛር ወንድምዋ ነበር። ስለዚህም እኅቶቹ “ጌታ ሆይ! እነሆ የምትወደው ታሞአል፤” ብለው ወደ እርሱ ላኩበት። ኢየሱስም ሰምቶ “ይህ ሕመም ለሞት አይሰጥም፤ ይልቁንም ለእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ነው” አለ። ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን እንዲሁም አልዓዛርን ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያንጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ይሁዳ እንደገና እንሂድ፤” አላቸው። ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ በድጋሚ ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “በቀን ውስጥ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ይገኙ የለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል፤” አላቸው። ይህንንም ከተናገረ በኋላ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! ተኝቶ እንደ ሆነስ ይድናል፤” አሉት። ኢየሱስ ግን ስለ ሞቱ ነበር የተናገረው፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያንጊዜ ኢየሱስ በግልጥ “አልዓዛር ሞተ፤ እናንተ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ፤” አላቸው። ዲዲሞስ የሚሉትም ቶማስ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛም እንሂድ፤” አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደመጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሣል፤” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ ከእርሷም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” ዓለም። እነርሱም “ጌታ ሆይ! መጥተህ እይ፤” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህም አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ፤” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ “የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች እንደ ከፈተ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስም በድጋሚ በጥልቅ ኀዘን ተውጦ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡ፤” አለ። የሞተውም ሰው እኅት ማርታ “ጌታ ሆይ! ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል፤” አለችው። ኢየሱስ “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር እንደምታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዐይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ፤” ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር ሆይ! ና፥ ወደ ውጭ ውጣ፤” ብሎ ጮኸ። ሞቶ የነበረውም ሰው እጆቹና እግሮቹ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ፤ ተዉት፤” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ሸንጎ ሰብስበው እንዲህ አሉ፥ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶችን ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንንና ወገናችንንም ይወስዳሉ፤” በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንደሚሻል አታስቡም፤” አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ። ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።
የዮሐንስ ወንጌል 11 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 11:1-54
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች