የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 10:7-30

የዮሐንስ ወንጌል 10:7-30 መቅካእኤ

ኢየሱስም ደግሞ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፤ ይገባልም፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ለሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወትን እንዲያገኙ፥ የተትረፈረፈ ሕይወትን እንዲያገኙ መጣሁ፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑት ተቀጣሪው ግን፥ ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል፤ በጎቹንም ይበትናቸዋል። ተቀጣሪ ስለሆነ፥ ለበጎቹም ስለማይገደው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ የእራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የእራሴም በጎች ያውቁኛል። አብም እንደሚያውቀኝ፥ እኔም አብን እንደማውቀው፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ማምጣት ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ አንድም መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለመውሰድ ነፍሴን አሳልፌ ስለምሰጥ አብ ይወደኛል። እኔ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመውሰድም ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ከእነኚህ ቃላት የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎች “ጋኔን አለበት፤ አብዶአልም፤ ለምንስ ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም “ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ሥውሮችን ዐይን ሊከፍት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ወቅቱም የብርድ ጊዜ ነበር። ኢየሱስም በመቅደስ፥ በሰሎሞን ታዛ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከብበው “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጥ ንገረን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን አታምኑም፤ እኔ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ሥራዎች ስለ እኔ ይመሰክራሉ፤ እናንተ ግን ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለምም አይጠፉም፤ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።”

Free Reading Plans and Devotionals related to የዮሐንስ ወንጌል 10:7-30