ትንቢተ ኤርምያስ 46

46
በግብጽ ላይ የተደረገ ፍርድ
1ስለ አሕዛብ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው።
2 # ኢሳ. 19፥1-25፤ ሕዝ. 29፥1—32፥32። ስለ ግብጽ፤ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በከርከሚሽ ስለ ነበረው፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታው ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ኒካዑ ሠራዊት።
3ጋሻንና አላባሽን አዘጋጁ ወደ ጦርነትም ቅረቡ። 4ፈረሰኞች ሆይ! ፈረሶችን ለጉሙና ውጡ፥ ራስ ቁርንም ደፍታችሁ በቦታችሁ ቁሙ፤ ጦርንም ሰንግሉ ጥሩርንም ልበሱ። 5ፈርተው ወደ ኋላ ሲመለሱ፥ ኃያላኖቻቸውም ሲደበደቡ ወደ ኋላቸውም ሳይመለከቱ ፈጥነው ሲሸሹ ለምን አየሁ? በዚህና በዚያ ድንጋጤ አለ፥ ይላል ጌታ። 6ፈጣኑ መሸሽ አይችልም ኃያሉም አያመልጥም፤ በሰሜን በኩል ባለው በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ እነርሱ ተሰናክለው ወደቁ። 7እንደ ግብጽ ወንዝ የሚነሣ፥ ውኃውም እንደ ወንዞች የሚናወጥ ይህ ማን ነው? 8ግብጽ እንደ ግብጽ ወንዝ ይነሳል ውኃውም እንደ ወንዞች ይናወጣል፤ እርሱም፦ እነሣለሁ ምድርንም ሁሉ እሸፍናለሁ፤ ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን አጠፋለሁ ብሏል። 9ፈረሶች ሆይ! ውጡ፤ ሰረገሎችም ሆይ! ንጐዱ፤ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የፉጥ ኃያላን፥ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኃያላን ይውጡ። 10ያ ቀን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን ነው፤ እርሱም ጠላቶቹን የሚበቀልበት የበቀል ቀን ነው፤ ሰይፍ በልቶ ይጠግባል በደማቸውም ይሰክራል፥ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መሥዋዕት አለውና። 11ድንግሊቱ የግብጽ ልጅ ሆይ! ወደ ገለዓድ ውጪ የሚቀባንም መድኃኒት ውሰጂ፤ ብዙ መድኃኒቶችን የተጠቀምሺው በከንቱ ነው፤ ለአንቺ መዳኛ የለሽም። 12ኃያሉ በኃያሉ ላይ ተሰናክሎ ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ ውርደትሽን ሰምተዋል፥ ልቅሶሽም ምድርን ሞልቶአታል።
ባቢሎን ግብጽን እንደምትወጋ
13 # ኤር. 43፥10-13። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንደሚመጣና የግብጽን ምድር እንደሚመታ ጌታ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
14በግብጽ አውጁ፥ በሚግዶልም አሰሙ፥ በሜምፎስና በጣፍናስ አሰሙ፤ እናንተም፦ ሰይፍ በዙሪያህ ያለውን በልቶአልና ተነሥ ራስህንም አዘጋጅ በሉ። 15ኃይለኞችህ ስለምን ተወገዱ? ጌታ ገፍቶአቸዋልና አልቆሙም። 16እርሱም ብዙዎችን አሰነካከለ፥ እርሱም ደግሞ ወደቀ፤ እርስ በርሳቸውም፦ ተነሡ፥ የአስጨናቂው ሰው ከሆነው ሰይፍ ፊት ወደ ወገናችን ወደ ተወለድንባትም ምድር እንመለስ ተባባሉ። 17በዚያም የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን፦ ሰዓቱን የሚያሳልፍ ለፍላፊ ብለው ጠሩት። 18እኔ ሕያው በመሆኔ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የተባለው ንጉሥ፥ በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር፥ በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፥ እንዲሁ በእውነት ይመጣል። 19አንቺ በግብጽ የምትቀመጪ ሴት ልጅ ሆይ! ሜምፎስ ባድማ ትሆናለችና፥ ትቃጠላለችምና፥ የሚቀመጥባትም አይገኝምና በምርኮ ስለምትሄጂ ዕቃዎችሽን አሰናጂ። 20ግብጽ እጅግ የተዋበች ጊደር ናት፤ ነገር ግን የቆላ ዝንብ ከሰሜን በኩል ይመጣባታል። 21በእርሷም መካከል ያሉ ቅጥረኛ ወታደሮችዋ እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤ የጥፋታቸው ቀንና የመጐብኘታቸው ጊዜ መጥቶባቸዋልና ተመለሱ፥ በአንድነትም ሸሹ፥ አልቆሙምም። 22“ጠላቶችዋ በኃይል ዘምተው እንደ እንጨት ቈራጮች በምሳር ይመጡባታልና በደረቱ እንደሚሽሎኮሎክ እባብ ድምፅ ታሰማለች። 23እነርሱ ስፍር ቊጥር የላቸውምና ከአንበጣም ይልቅ ብዙ ናቸውና የማያሳልፍ ጥቅጥቅ ቢሆንም እንኳ የዱርዋን ዛፎች ይቈርጣሉ፥ ይላል ጌታ። 24የግብጽ ሴት ልጅ ታፍራለች፤ ለሰሜኑ ሕዝብ ተላልፋ በእጃቸው ትሰጣለች።” 25የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ፤ 26ነፍሳቸውንም በሚሽዋት ሰዎች እጅ፥ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፥ በባርያዎቹም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ አንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ።
ጌታ እስራኤልን ያድናል
27 # ኤር. 30፥10፤11። “ነገር ግን አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ! አትፍራ፥ አንተም እስራኤል ሆይ! አትደንግጥ፤ እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረከባት ምድር አድናለሁና፤ ያዕቆብም ተመልሶ ያርፋል በደኅንነትም ይቀመጣል፥ እርሱንም ማንም አያስፈራውም። 28አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ይላል ጌታ፤ አንተንም እንድትሰደድ ያደረግኹባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ እንደጥፋትህ መጠን እቀጣሃለሁ እንጂ ያለ ቅጣት ከቶ አልተውህም።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ