ትንቢተ ኤርምያስ 43

43
ነቢዩ ኤርምያስ ፍርድ እንደሚመጣ ማስጠንቀቁ
1ለእነርሱ አምላካቸው እግዚአብሔር የላከውን ይህን የአምላካቸውን የጌታን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ መናገርን በፈጸመ ጊዜ፥ 2የሆሻያ ልጅ ዓዛርያስ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ትዕቢተኞችም ሰዎች ሁሉ ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “ሐሰት ተናግረሃል፤ ጌታ አምላካችን፦ ‘በዚያ ለመቀመጥ ወደ ግብጽ አትግቡ’ ብሎ እንድትናገር አልላከህም፤ 3ነገር ግን ከለዳውያን እንዲገድሉን ወደ ባቢሎንም ማርከው እንዲወስዱን በእጃቸው አሳልፈህ ልትሰጠን የኔርያ ልጅ ባሮክ በላያችን ላይ አነሣሥቶሃል።” 4የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ የጌታን ድምፅ አልሰሙም። 5#2ነገ. 25፥26።የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ ከተሰደዱባቸው ከአሕዛብ ስፍራዎች ሁሉ የተመለሱትን የይሁዳን ትሩፍ ሁሉ፥ 6ወንዶችንና ሴቶችን ልጆችንም ሕፃናትንም የንጉሡንም ሴቶች ልጆች፥ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከሳፋን ልጅ ከአኪቃም ልጅ ከጎዶልያስ ጋር የተዋቸውን ሰዎች ሁሉ፥ ነቢዩንም ኤርምያስን የኔርያንም ልጅ ባሮክን ወሰዱ፤ 7የጌታንም ድምፅ አልሰሙምና ወደ ግብጽ ምድር ገቡ፥ እስከ ጣፍናስ ድረስ መጡ።
8በጣፍናስም የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9“ትላልቅ ድንጋዮች በእጅህ ውሰድ፥ የይሁዳም ሰዎች እያዩ በጣፍናስ በፈርዖን ቤት መግቢያ ባለው በቅጥራኑና በጡቡ ደጃፍ ሸሽጋቸው፤ 10እንዲህም በላቸው፦ ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ልኬ ባርያዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን አመጣለሁ፥ ዙፋኑንም እኔ በሸሸግኋቸው በእነዚህ ድንጋዮች ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም የዙፋኑን ድንኳን በላያቸው ይዘረጋል። 11መጥቶም የግብጽን ምድር ይመታል፥ ለሞትም የሚሆነውን ለሞት፥ ለምርኮም የሚሆነውን ለምርኮ፥ ለሰይፍም የሚሆነውን ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል። 12በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን አነድዳለሁ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ያቃጥላቸዋል ይማርካቸዋልም፤ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፤ ከዚያም ስፍራ በሰላም ይወጣል። 13በግብጽም ምድር ያለውን የሄልዮቱን ከተማ ሐውልቶች ይሰብራል፥ የግብጽንም አማልክት ቤቶች በእሳት ያቃጥላል።’ ”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ