ትንቢተ ኤርምያስ 37
37
የሴዴቅያስ ከንቱ ተስፋ
1 #
2ነገ. 24፥17፤ 2ዜ.መ. 36፥10። የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ምድር ላይ ያነገሠው የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፋንታ ነገሠ። 2በነቢዩ በኤርምያስም በኩል የተናገረውን የጌታን ቃላት እርሱም ሆነ ባርያዎቹ የአገሩም ሕዝብ አልሰሙም።
3ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ “እባክህ፥ ወደ አምላካችን ወደ ጌታ ስለ እኛ ጸልይ” ብሎ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ። 4እርሱንም ወደ እስር ቤት ገና አላስገቡትም ነበርና ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይወጣና ይገባ ነበር። 5የፈርዖንም ሠራዊት ከግብጽ ወጣ፤ ኢየሩሳሌምንም ከብበዋት የነበሩ ከለዳውያን ይህን ወሬ በሰሙ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ተመለሱ።
6የጌታም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 7“የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔን እንድትጠይቁኝ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ ‘እነሆ፥ ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብጽ ይመለሳል። 8ከለዳውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይዋጉአታል ይይዟታልም በእሳትም ያቃጥሉአታል። 9ጌታ እንዲህ ይላል፦ አይሄዱምና፦ “ከለዳውያን በእርግጥ ከእኛ ዘንድ ይሄዳሉ” ብላችሁ ራሳችሁን አታታሉ። 10እናንተንም የሚወጉዋችሁን የከለዳውያንን ሠራዊት ሁሉ ድል ብታደርጉ እንኳ ከእነርሱም መካከል የቆሰሉ ሰዎች ብቻ ቢቀሩ፥ እነርሱም ሁሉ ከየድንኳኖቻቸው ይነሣሉ ይህችንም ከተማ በእሳት ያቃጥላታል።’ ”
የነቢዩ ኤርምያስ መታሰር
11የፈርዖንም ሠራዊት ከመቃረቡ የተነሣ የከለዳውያን ሠራዊት ከኢየሩሳሌም ተመልሶ በነበረ ጊዜ፥ 12ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን ድርሻ ከዚያ ለመቀበል ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ከኢየሩሳሌም ወጣ። 13በብንያምም በር በነበረ ጊዜ የሐናንያ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የሪያ የተባለ የዘበኞች አለቃ በዚያ ነበረ፤ እርሱም ነቢዩን ኤርምያስን፦ “ወደ ከለዳውያን ልትኰበልል ነው” ብሎ ያዘው። 14ኤርምያስም፦ “ሐሰት ነው፤ ወደ ከለዳውያን መኰብለሌ አይደለም” አለ፤ የሪያም ግን አልሰማውም፥ ኤርምያስንም ይዞ ወደ አለቆች አመጣው። 15አለቆችም ተቈጥተው ኤርምያስን መቱት፥ የጸሐፊውንም የዮናታንን ቤት የእስር ቤት አድርገውት ነበርና በዚያ ቤት አስረው አኖሩት።
16ኤርምያስም በጉድጓድ ውስጥ ለውኃ ማከማቻ ወደሚሆን ቤት ወደ ጓዳዎቹ ገባ፤ እርሱም በዚያ ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ፥ 17ንጉሡ ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፥ ንጉሡም በቤቱ፦ “በውኑ ከጌታ ዘንድ የሆነ ቃል አለን?” ብሎ በድብቅ ጠየቀው። ኤርምያስም፦ “አዎን አለ” ብሎ መለሰ። ከዚያም በኋላ፦ “በባቢሎን ንጉሥ እጅ ተላልፈህ ትሰጣለህ” አለ። 18ኤርምያስም ደግሞ ንጉሡን ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ “በእስር ቤት የጣላችሁኝ አንተን ወይስ ባርያዎችህን ወይስ ይህን ሕዝብ ምን በድያችሁ ነው? 19‘የባቢሎን ንጉሥ በእናንተና በዚህች አገር ላይ አይመጣም’ ብለው ትንቢት ለእናንተ ይናገሩ የነበሩ ነብዮቻችሁ ወዴት አሉ? 20ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! እንድትሰማኝ አሁን እለምንሃለሁ፤ እባክህ፥ ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ።” 21ንጉሡም ሴዴቅያስ አዘዘ፥ ኤርምያስንም በእስር ቤት አደባባይ አኖሩት፥ እንጀራም ሁሉ ከከተማይቱ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ ይሰጡት ነበር። እንዲሁም ኤርምያስ በእስር ቤት አደባባይ ተቀምጦ ነበር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 37: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ