ትንቢተ ኤርምያስ 35

35
ሬካባውያን መመስገናቸው
1 # 2ነገ. 23፥36—24፥6፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7። በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦ 2“ወደ ሬካባውያን ቤት ሂድና አነጋግራቸው፥ ወደ ጌታም ቤት ከጓዳዎቹ ወደ አንዱ አስገባቸው የወይን ጠጅም እንዲጠጡ ስጣቸው።” 3የከባስን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያን፥ ወንድሞቹንም፥ ልጆቹንም ሁሉ፥ የሬካባውያንን ወገን ሁሉ ወሰድኩ፤ 4ወደ ጌታም ቤት የደጁ ጠባቂ በሆነው በሰሎም ልጅ በመዕሤያ ጓዳ በላይ ባለው በአለቆች ጓዳ አጠገብ ወደሚገኘው፥ ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ጌዴልያ ልጅ ወደ ሐናን ልጆች ጓዳ አስገባኋቸው። 5ከዚያም በሬካባውያን ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አስቀምጬ፦ “የወይኑን ጠጅ ጠጡ” አልኳቸው። 6እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፦ “የወይኑን ጠጅ አንጠጣም፥ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናልና፦ ‘እናንተና ልጆቻችሁ ለዘለዓለም የወይን ጠጅ አትጠጡ፤ 7በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፥ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፥ ዘርንም አትዝሩ፥ ወይንን አትትከሉ ወይም የወይን ቦታ አይኑራችሁ።’ 8እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ሰምተን፥ ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል፤ እኛም ሚስቶቻችንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም፤ 9የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም፤ የወይን ቦታና እርሻ ዘርም የለንም፤ 10ሆኖም ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጠናል፥ እኛም በመታዘዝ አባታችን ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ አድርገናል። 11ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደዚህች ምድር በመጣ ጊዜ፦ ‘የከለዳውያንን ሠራዊትና የሶርያውያንን ሠራዊት በመፍራት ኑ ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ’ አልን፤ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን።”
12የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ቃሎቼን ለመስማት ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል ጌታ። 14የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹን የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ያዘዛቸው ቃላት ተፈጸሙ፤ ለአባታቸውም ትእዛዝ ታዝዘዋልና እስከ ዛሬ ድረስ አይጠጡም፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ተናገርኋቸው፤ ተናገርሁ፥ ሆኖም ግን አልሰማችሁኝም። 15እንዲሁም፦ ‘እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ ሥራችሁንም አሳምሩ፥ ልታገለግሉአቸውም ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ’ እያልሁ በማለዳ ተነሥቼ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ላክሁባችሁ፤ ላክሁ፥ እናንተ ግን ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም እኔንም አልሰማችሁኝም። 16የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ልጆች አባታቸው ያዘዛቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋል፥ ይህ ሕዝብ ግን አልሰማኝም። 17ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሆነ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በተናገርኋቸው ጊዜ አልሰሙምና፥ በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝምና በእነርሱ ላይ የተናገርኩትን ክፉ ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በተቀመጡ ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ።”
18ኤርምያስም ለሬካባውያን ቤት እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለአባታችሁ ለኢዮናዳብ ትእዛዝ ታዝዛችኋልና፥ ትእዛዛቱንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፥ ያዘዛችሁንም በሙሉ ፈጽማችኋልና፤ 19ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በፊቴ የሚቆም ሰው ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘለዓለም ፈጽሞ አይታጣም።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ