የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 18

18
ሸክላ ሠሪው እና ሸክላው
1ከጌታ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦ 2“ተነሣ፥ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፥ በዚያም ቃሌን አሰማሃለሁ።” 3ወደ ሸክላ ሠሪው ቤትም ወረድሁ፥ እነሆም፥ ሥራውን በመንኰራኵር ላይ ይሠራ ነበር። 4ከጭቃም ይሠራው የነበረ ዕቃ በሸክላ ሠሪው እጅ ተበላሸ፥ ሸክላ ሠሪውም እንደ ወደደ መልሶ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው።
5የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 6“የእስራኤል ቤት ሆይ! ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ላይ መሥራት አልችልምን? ይላል ጌታ፤ እነሆ፥ ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ፥ የእስራኤል ቤት ሆይ! እንዲሁ እናንተ በእኔ እጅ አላችሁ። 7በሕዝብና በመንግሥት ላይ እንደምነቅል እንደማፈርስም እንደማጠፋም በተናገርሁ ጊዜ፥ 8ይህ ስለ እርሱ የተናገርሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፥ እኔ ላደርግበት ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ። 9በሕዝብና በመንግሥት ላይ እንደምሠራና እንደምተክል በተናገርሁ ጊዜ፥ 10በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ ድምፄንም ባይሰማ፥ እኔ ላደርግለት ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ። 11አሁን እንግዲህ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር እፈጥርባችኋለሁ፥ አሳብንም አስብባችኋለሁ፤ አሁንም ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ መንገዳችሁንና ሥራችሁንም አስተካክሉ’ ብለህ ተናገራቸው።
የእስራኤል ሕዝብ በእልከኛነቱ ጣዖትን ማምለኩ
12“እነርሱ ግን፦ ‘ተስፋ የለውም! አሳባችንን ተከትለን እንሄዳለን፥ ሁላችንም እንደ ክፉው ልባችን እልከኝነት እናደርጋለን’ አሉ።
13“ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ በአሕዛብ መካከል፦ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? ብላችሁ ጠይቁ። የእስራኤል ድንግል በጣም የሚያስደነግጠውን ነገር አድርጋለች። 14በውኑ የሊባኖስ በረዶ የድጋያማውን ምድር ይተዋልን? ወይስ ከሩቅ የምትመጣው ቀዝቃዛይቱ ፈሳሽ ውኃ ትደርቃለችን? 15ሕዝቤ ግን ረስተውኛል ለከንቱ ነገርም ዐጥነዋል፤ ከመንገዳቸውም አሰናክለዋቸዋል ከቀድሞውም ጐዳና ርቀው ወዳልተሠራው ወደ ጠማማው መንገድ ሄደዋል። 16ምድራቸውን ለመሣቀቂያና ለዘለዓለም ማፍዋጫ አድርገዋል፤ የሚያልፍባት ሁሉ ይደነቃል፥ ራሱንም ይነቀንቃል። 17በጠላት ፊት እንደ ምሥራቅ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፥ በጥፋታቸውም ቀን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም።”
በነቢዩ ኤርምያስ ላይ የተደረገ ሤራ
18እነርሱም፦ “ሕግ ከካህን፥ ምክርም ከጠቢብ፥ ቃልም ከነቢይ አይጠፋምና ኑ፥ በኤርምያስ ላይ ሤራን እናሢር። ኑ፥ በአንደበት እንምታው፥ ቃላቱንም ሁሉ አናድምጥ” አሉ።
19አቤቱ! አድምጠኝ፥ ጠላቶቼ ምን እደሚሉ ስማ። 20ለነፍሴ ጉድጓድ ቈፍረዋልና በውኑ በመልካም ፋንታ ክፉ ይመለሳልን? ስለ እነርሱ በመልካም ለመናገር ቁጣህንም ከእነርሱ ለመመለስ በፊትህ እንደ ቆምሁ አስታውስ። 21ስለዚህ ልጆቻቸውን ለራብ ስጥ፥ ለሰይፍም እጅ አሳልፈህ ስጣቸው፥ ሚስቶቻቸውም የወላድ መካንና መበለቶች ይሁኑ፥ ወንዶቻቸውም በሞት ይጥፉ፥ ጉልማሶቻቸውም በጦርነት ጊዜ በሰይፍ ይመቱ። 22ሊይዙኝ ጉድጓድ ቆፍረዋልና፥ ለእግሮቼም ወጥመድ ሸሽገዋልና ድንገት በላያቸው ጭፍራ ባመጣህ ጊዜ ከቤታቸው ጩኸት ይሰማ። 23አንተ ግን፥ አቤቱ! እኔን ለመግደል በላዬ የመከሩትን ምክር ሁሉ ታውቃለህ፤ በደላቸውን ይቅር አትበል፥ ኃጢአታቸውንም ከፊትህ አትደምስስ፤ በፊትህም ይውደቁ፥ በቁጣህ ጊዜ እንዲሁ አድርግባቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ